ሀገራቸውን በ67 ዓመት የሚበልጡት ጃማይካዊት የዓለማችን የረጅም እድሜ ባለፀጋ ተብለዋል

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 10፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የ117 ዓመት የእድሜ ባለፀጋ ጃማይካዊት አዛውንት የዓለማችን በህይወት ያሉ የረጅም እድሜ ባለቤት ተብለዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጣር በ1900 የተወለዱት ቪዮሌት ብራወን፥ ጃማይካ እንደ ሀገር ከመመስረቷ 67 ዓመት ቀድመው ነው የተወለዱት።

ታዲያ ሀገራቸውን በ67 ዓመት የሚበልጡትና የ117 ዓመት እድሜ ባለፀጋ የሆኑት እኚህ አዛውንት እንደ ጄሮንዮሎጀይ የጥናት ቡድን ገለጻ በህይወት ያሉ የዓለማችን የረጅም እድሜ ባለ ፀጋ ሆነዋል።

ቪዮሌት ብራወን ፥ “ረጅም እድሜ የመኖር ሚስጥር ጠንካራ ስራ ነው”፤ “እናት እና አባታችሁን አክብሩ እንዲህ ካደረጋችሁ እድሜያቹ ይረዝማል” ሲሉም መክረዋል።

በመልካም ጤንነት ላይ የሚገኙት አውንቷ ቪኦሌት በእርሻ ስራ ተሰማርተው ሕይወታውን ሲመሩ የነበረ ሲሆን፥ ስለ አመጋገባቸው ተጠይቀውም ከአሳማና ከዶሮ ስጋ በስተቀር ያገኙትን ሁሉ እንደሚበሉ ተናግረዋል።

የበራሂ (ጂን) ጉዳይ ሆኖ ቪዮሌት ብራወን ወንድ ልጅም የ97 አመት የእድሜ ባለጸጋ ለመሆን በቅተዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የ117 ዓመት ከ38 ቀን እድሜ ባለፀጋ የሆኑትን ቪዮሌት ብራወንን የዓለም የድንቃድንቅ እና ክብረወሰኖች መዝገብ በህይወት ያሉ የረጅም እድሜ ባለፀጋነት ማረጋገጫን ሰጥቷቸዋል።

የሀገሩቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር አንድሪው ሆልነስም በትዊተር ገጻቸው ለቪዮሌት ብራወን እንኳን አደረሰዎት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ከዚህ ቀደም በህይወት ያሉ የረጅም እድሜ ባለፀጋነት ክብረወሰን ባሳለፍነው ቅዳሜ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ጣሊያናዊቷ የ117 ዓመቷ አዛውንት ኤማ ሞራኖ እጅ ነበር።

ምንጭ፦ www.upi.com/Odd


በሙለታ መንገሻ