የቦስተን ማራቶን የመጀመሪያዋ ሴት ተወዳዳሪ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም ውድድሩ ላይ ተካፍለዋል

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 10፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1967 የሳይርኩስ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህር ክፍል ተማሪዋ የ20 ዓመት ወጣት በቦስተን ማራቶን ላይ የተካፈለች የመጀመሪያዋ ሴት በመሆን ታሪክ ሰራች።

የያኔዋ የ20 ዓመት ወጣት የዛሬዋ የ70 ዓመት አዛውንት ካትሪን ስዊዘር ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም በቦስተን ማራቶን በመካፈል አሁንም አዲስ ታሪክ ማስመግብ መቻላቸው ነው የተነገረው።

ስዊዘር ትናንት ምሽት በተካሄደው የቦስተን ማራቶን ላይ ከ50 ዓመት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ በቦስተን ማራቶን ላይ ለብሰው የሮጡትን የማልያ ቁጥር ለብሰው መወዳደራቸውም ተነግሯል።

ካትሪን ስዊዘር እስካሁን በ40 ማራቶኖች ላይ የሮጡ ሲሆን፥ በቦስተን ማራቶን ላይም ለ9ኛ ጊዜ መሳተፋቸው ነው የተነገረው።

የ70 ዓመቷ አዛውንት የትናንትናውን የቦስተን ማራቶን ለውሃ፣ ለቃለ መጠይቅ እና ለፎቶ ግራፍ ሩጫቸውን አቋርጠው እየቆሙም ቢሆን ውድድሩን በ4 ሰዓት ከ44 ደቂቃ ከ21 ሰከንድ ማጠናቀቅ ችለዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጣር በ1967 ሴቶች እንዳይሳተፉ በሚከለከልበት የቦስተን ማራቶን ሩጫ ላይ የስማቸውን ምህጻረ ቃል በመጠቀም ሸውደው የመወዳደሪያ ቁጥር ወስደው ነበር የሮጡት።

በወቅቱም በውድድሩ ላይ ሴት ተወዳዳሪ መኖሯ ከታወቀ በኋላ የውድድሩ አዛጋጆች ካትሪን ስዊዘር ውድድሩን እንድታቆም ሲያስገድዱ ነበር።

አዘጋጆቹ በወቅቱ ሲያደርጉት የነበረውን ድርጊት የሚያሳይ ምስልም የተለቀቀ ሲሆን፥ በምስሉ ላይም አዘጋጆቹ ካትሪንን ሲገፈታትሩ እና ሲያባርሩ ተስተውሏል።

Swithet_2.jpg

ካትሪን ስዊዘር ይናገራሉ፥ “ከ50 ዓመት በፊት በቦስተን ጎዳና ላይ ያጋጠመኝ ክስተት የእኔን እና የሌሎችን ሴቶች ህይወት ሙሉ በሙሉ የቀየረ ነው”።

“ዛሬ ያደረኩት ሩጫም በቦስተን ማራቶን ላይ የተካፈልኩበትን 50ኛ ዓመት ለማክበር እና ቀጣይ 50 ዓመታት የተሻሉ እንሆኑ ለማድረግ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

ምንጭ፦ http://edition.cnn.com

በሙለታ መንገሻ