17 ኪሎ ግራም የምትመዝነው የስምንት ወር ጨቅላ ጉዳይ ዶክተሮችን አስጨንቋል

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 9 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ህንዳዊቷ ቻሃት ኩማር የስምንት ወር ጨቅላ ህጻን ስትሆን ስትወለድ ጤነኛ ህጻን እንደነበረች ወላጆቿ ይናገራሉ።

ጨቅላዋ እስከ አራት ወሯ ድረስም የተስተካከለ ሰውነት ነበራት።

ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያት ግን ባልተለመደ መልኩ የሰውነቷ ክብደት መጨመሩን ነው ወላጆቿ የሚናገሩት።

በአራት ወራት ውስጥ የታየው ለውጥም አሁን ላይ ለሰውነት ክብደቷ መጨመር ምክንያት ሆኗል።

በዚህ እድሜዋ 38 ፓውንድ ወይም 17 ነጥብ 2 ኪሎ ግራም ትመዝናለች።

ይህ ሁኔታዋ ደግሞ ቤተሰቦቿን አስጨንቋል፤ ጤነኛዋ ጨቅላ ህጻን ከልክ በላይ መወፈሯና አሁንም አሁንም ምግብ አምጡ ማለቷ ችግር ቢኖር ነው እያሉም ነው።

ምግብ ቶሎ ቶሎ ካልተመገበችም እንደምታለቅስ ወላጅ አባቷ ሱራጅ ቻሃት ይናገራል።

ቻሃት ረዘም ላለ ጊዜ በርካታ መጠን ያለው ምግብን በመመገብ ጊዜዋን ታሳልፋለች።

ሁኔታው የፈጣሪ ስራ ነው ያለው ወላጅ አባቷ፥ መፍትሄ ለመስጠት ከአቅማቸው በላይ እንደሆነባቸው ይናገራል።

እናቷ ሬናም ልጃቸው አስፈላጊውን ህክምና እንድታገኝ ለማድረግ አቅም እንደሌላቸው ትገልጻለች።

የወፊት ህይወቷ መልካም እንዲሆን ምኞቷ መሆኑንም ነው የገለጸችው።

ሁኔታውን ለመረዳት የሞከሩት ዶክተሮች እስካሁን ምንም አይነት ፍንጭ አላገኙም።

የጨቅላዋ ሁኔታም አሁን ላይ ለእነርሱ አስጨናቂ ሆኗል፤ መፍትሄ ፍለጋ ቢኳትኑም ተፈጥሮዋ ሁኔታውን አስቸጋሪ አድርጎባቸዋል።

ጉዳዩን የተከታተሉት ዶክተር ሻርማ፥ ጉዳዩ በፍጥነት እልባት ማግኘት እንዳለበት ተናግረዋል።

ይሁን እንጅ የቤተሰቦቿ የኑሮ ሁኔታ ጨቅላ ህጻኗ ህክምናውን እንዳታገኝ አድርጓታልም ይላሉ።

እንደ እርሳቸው ገለጻ የስምንት ወሯ ቻሃት እንደ 10 አመት ታዳጊ ህጻን ትመገባለች፤ ሁኔታው እንዲስተካከል ግን የምግብ ፍጆታዋን ልትቀንስ ይገባል ነው ያሉት።

የህጻኗን ችግር ለማወቅ የሚያስችለውን የደም ናሙና ለመውሰድ የተደረገው ጥረትም፥ በቻሃት ቆዳ መወፈርና መጠንከር ምክንያት እስካሁን አልተሳካም።

 

 

 


ምንጭ፦ foxnews.com