የባቡር መስመሯን 19 ወለል ባለው ህንጻ ውስጥ እንዲያልፍ ያደረገቺው ከተማ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 11 ፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቻይና ደቡብ ምስራቅ የምትገኘው ቾንግቺንግ ከተማ 19 ወለል ባለው አንድ ህንጻዋ ውስጥ የቀላል ባቡሯን መስመር ዘርግታለች፡፡

ነዋሪዎቿም በህንጻው ውስጥ ከስድስተኛ እስከ ስምንተኛ ወለል ድረስ በመሄድ ሊዚባ የባቡር ጣቢያ ላይ መሳፈር ይችላሉ፡፡

በዚህች ከተማ በጣም በተጨናነቀ ሁኔታ በ31 ሺህ ስኩየር ማይል ውስጥ 49 ሚሊየን ሰዎች ይኖራሉ፡፡

የከተማዋ የትራንስፖርት ቢሮ ቃል አቀባይ ከተማዋ ያለችበት ተፈጥሯዊ ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ በመሆኑ፥ ለባቡር እና ለሌሎች ትራንስፖርት የሚሆን ክፍት መንገድ ለመስራት ፈታኝ ነበር ብለዋል፡፡

በከተማዋ ያለውን የቦታ ጥበት በአግባቡ ለመጠቀም ሲባል፥ የቀላል ባቡር መስመሩ በከተማዋ ባለ19 ወለል ህንጻ ውስጥ እንዲያልፍ ሆኖ ነው የተሰራው፡፡

የከተማዋ የፕላን አውጭዎች በህንጻዎች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የባቡር መስመር ቁጥር ሁለት በተባለው አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ አድርገው ነው መስመሩን የሰሩት፡፡

chongqing.jpg

ባቡሩ በሚያልፍባቸው መስመሮች አካባቢ ያሉ የህንጻው ነዋሪዎችን ከድምፅ ብክለት ለመጠበቅ የድምፅ ማፈኛ መሳሪያዎች መተከላቸው ተነግሯል፡፡

የባቡሩ ድምፅም ከመመገቢያ እቃ ማጠቢያ ማሽን ድምፅ በላይ እንዳይሆን እና ነዋሪዎችን እንዳይረብሽ ታስቦ ነው የተሰራው፡፡

ቾንግቺንግ እንደ ቤጂንግ፣ ሻንጋይ እና ቲያንጅን ሁሉ በማዘጋጃ ቤት ማዕከልነቷ አራተኛዋ ከተማ ስትሆን፥ በያንገቲዝ ወንዝ ዳርቻ ትገኛለች፡፡

ይህቺ ከተማ የተራራ መዲና የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቷታል፤ ምክንያቱም የተመሰረተችበት ስፍራ ተራራማ በመሆኑ ነው፡፡

 

 

 

ምንጭ፡-www.dailymail.co.uk/