የህክምና እርዳታ ፍለጋ ለፖሊስ የደወለው ቤት በርባሪ በቁጥጥር ስር ውሏል

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 11 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካዋ ቨርጅኒያ ግዛት ነዋሪ የሆነው የ21 አመቱ ወጣት ራሱ ባመጣው ጣጣ እቅዱን ሳያሳካ ተመልሷል።

ወጣቱ በዚች ግዛት ፌር ፋክስ አካባቢ በሚገኝ አንድ አፓርታማ በማምራት አንደኛውን ቤት ሰብሮ በመግባት ለዝርፊያ ይሰማራል።

ቤት ውስጥ ከገባ በኋላም የያዘውን ይዞ ወዲያ ወዲህ ሲል አጋጣሚ የቤቱ ባለቤት በአካባቢው ይደርሳል።

ከመያዝ ለማምለጥ የነበረው ብቸኛ እድል መዝለል ነበርና ከቤቱ በረንዳ ወደታች ይዘላል።

በዚህ ጊዜ እግሩ የመሰበር አደጋ ያጋጥመውና የያዘውን ይዞ ከአካባቢው መራቅ ባለመቻሉ አንድ ቦታ አረፍ ብሎ የእርዳታ ጥሪውን ያስተላልፋል።

ወደ አካባቢው ፖሊስ በመደወልም “እግሬ ተሰብራልና የድረሱልኝ” ጥሪውን አስተላልፏል።

ፖሊሶቹ ወደ አካባቢው ሲደርሱ እርሱ ድረሱልኝ ካለበት አቅራቢያ ቤት መበርበሩን ይሰማሉ።

ጉዳዩን ከሰሙ በኋላም ድረሱልኝ ወዳለው ወጣት መገኛ አምርተው ካገኙት በኋላ ወደ ህክምና ተቋም ይወስዱታል።

በወቅቱ በአካባቢው በረዶ ጥሎ ስለነበርም ከዘረፈው ቤት እስከተደበቀበት ቦታ ድረስ ሲራመድ የእግር ኮቴው አሻራ አርፏል።

ይህ ደግሞ የዝርፊያው ፈጻሚ እርሱ ስለመሆኑ ማስረጃ በመሆኑ ፖሊሶቹ ሳይወጡ ሳይወርዱ ተፈላጊውን ወንጀለኛ በህክምና እርዳታ ጥሪ ሰበብ አግኝተውታል።

በዚህ ሳቢያም ታክሞ ከወጣ በኋላ በዝርፊያ ወንጀል ተከሶ ተገቢውን ፍርድ ያገኛል ተብሏል።

ምንጭ፦ አሶሺየትድ ፕረስ