የኒው ዮርክ ፍርድ ቤት በሁለት ዝንጀሮዎች ጉዳይ ላይ ውሳኔ ሊሰጥ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ዝንጀሮዎች ልክ እንደ ሰው በህጋዊ መብቶች ፍርድ ቤት ቀርበው ሊዳኙ ይችሉ ይሆን?

የእንስሳት መብት ጉዳይ ተሟጋች ቡድን እና ሰብዓዊ ያልሀጎኑ መብቶች ፕሮጄክት ተወካዩ ጠበቃ ስቲቨን ዋይዝ በማንሃታን ከተማ የሚገኘውን ችሎት በዚሁ ጉዳይ ላይ ለማሳመን እየሞገቱ ነው።

ጠበቃው ስቲቨን ዋይዝ ቶሚ እና ኪኮ የተባሉ ሁለት ዝንጀሮዎች ተቆልፎባቸው ከሚኖሩበት የብረት አጥር ቤት ነፃ በመውጣት እንዲኖሩ ነው የሚከራከሩት።

ዋይዝ የዝንጀሮዎቹ ጉዳይ ፍርድ ቤት እንዲደርስ ለዓመታት ብዙ ያልተሳኩ ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን፥ ሙከራቸውም በህገ ወጥ መንገድ ታስረዋል የሚሏቸውን ዝንጀሮዎች ነፃ ለማውጣት ነው።

እንደ ጠበቃ ዋይዝ ገለፃ፥ በችሎቱ ፊት ያልቀረቡት ዝንጀሮዎቹ የተሻለ ኑሮ መኖር አለባቸው።

ፍርድ ቤቱ ጠበቃው ባቀረቡት ሀሳብ የሚስማማ ከሆነም ዝንጀሮዎቹ ከዝርያዎቻቸው ጋር ተቀላቅለው እንዲኖሩ ይደረጋል ነው የተባለው።

የኒው ዮርክ ፍርድ ቤት የአምስት ዳኞች ጉባዔም በጉዳዩ ላይ በሁለት ቀናት ውስጥ አሊያም በአንድ ሳምንት ውስጥ ውሳኔ እንደሚሰጥበት እየተጠበቀ ነው።

ምንጭ፦ theprimatesanctuary.com