ሴራሊዮናዊው ቄስ ግዙፍ አልማዝ ማግኘታቸው ተነግሯል

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 8 ፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሴራሊዮናዊው ቄስ ኢማኑኤል ሞሞ በኮኖ አካባቢ 709 ካራት የሚመዝን አልማዝ ማግኘታቸው እየተነገረ ነው፡፡

ቄሱ ያገኙት አልማዝ በግዝፈቱም በዓለማችን ከተገኘኙ በግዙፍነታቸው ከሚጠቀሱ 20 አልማዞች አንዱ መሆኑም ተጠቅሷል።

አልማዙ በሴራሊዮን በክብደቱ የመጀመሪያው ሊሆን አልቻለም፤ ምክንያቱም በፈረንጆች 1972 በዚያው ሀገር 969 ካራት የሚመዝን አልማዝ ተገኝቶ ስለነበር ነው፡፡

ሰሞኑን የተገኘው ይህ አልማዝ በዓለማችን ከተገኙት ውስጥ በግዝፈቱ 13ኛ ሆኖ ተመዝግቧል ነው የተባለው፡፡

የአልማዝ መአድኑ ከወንዝ እንደተገኘ ወደ ሴራሊዮን ፕሬዚዳንት ኧርነስት ባ ኮሮማ ተወስዷል፡፡

ፕሬዚዳንቱ የአካባቢውን አመራሮች አልማዙ ወደ ውጭ ሀገር በህገወጥ ሳይወጣ በማምጣታቸው አመስግነዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜም በሴራሊዮን ማዕከላዊ ባንክ ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል፡፡

አልማዙን ያገኙት ቄስም የሚገባቸውን የሚደረግላቸው ሲሆን፥ የአልማዙ ንብረትነትም ለሀገሪቱ ይሆናል ነው ያሉት፡፡

በዓለማችን ከዚህ ቀደም የተገኙ ትላልቅ አልማዞች በካራት ተመዝነው ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ደረጃ የያዙት የሚከተሉት ናቸው፡፡

አንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው በደቡብ አፍሪካ በ1905 የተገኘው ኩሊያን አልማዝ 3 ሺህ 107 ካራት የሚመዝነው ሲሆን፥ በቦትስዋና በ2015 የተገኘው ሌሴዲ ላሮና 1 ሺ 111 ካራት በመመዘን ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

በደቡብ አፍሪካ በ1893 የተገኘው ኤክሰልሲየር አልማዝ በ995 ካራት ሶስተኛ ላይ ሲቀመጥ፥ በሴራሊዮን በ1972 የተገኘው የሴራሊዮን ኮከብ የተሰኘው አልማዝ 969 ካራት በመመዘን አራተኛ ላይ ተቀምጧል፡፡

አምስተኛ ደረጃ የተሰጠው ደግሞ በዴሞክራቲክ ኮንጎ በ1984 የተገኘው እና ወደር የለሽ የተሰኘው አልማዝ ሲሆን 890 ካራት ክብደት ይመዝናል፡፡

 

 

 

ምንጭ፡-ቢቢሲ