ስለ ሰው ወዳጆቹ ውሻዎች ያልተሰሙ አስገራሚ እውነታዎች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ውሻዎች በርካታ ከሰው ልጅ ጋር የሚያመሳስል ባህሪ አላቸው።

በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የተደረገ ጥናት ውሻዎች እነደ ሰው ሁሉ እንደሚቀኑ አረጋግጫለሁ ብሏል።

14 የተለያየ ዝርያ ያላቸው 36 ውሻዎች ላይ የተደረገው ምርምር ውሻዎችን ምርጥ ጓደኛችን እስካደረግናቸው ድረስ በየጊዜው አዳዲስ ነገሮችን ያሳዩናል ይላል።

ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን የውሻዎች አስገራሚ እውነታዎች ምናልባትም ስምተዋቸው ላያውቁ ይችላሉ።

1. ውሻዎች የጥፋተኝነት ስሜት አይሰማቸውም

ውሻዎች የቅናት ስሜት ሲሰማቸው የአይናቸው ቀለም እንደሚቀየር በጥናቱ ቢረጋገጥም ይህ ግን የጥፋተኝነት ስሜት እንደተሰማቸው አያሳይም ተብሏል።

ውሻዎች እንዳይመገቡ የተነገራቸውን ነገር ሲመገቡ ባለቤቶቻቸው ሲቆጧቸው ወዲያውኑ ጥፋተኝነት እነደተሰማቸው ለማሳየት ቢሞክሩም መልሰው ሲያጠፉ ይስተዋላል።

2. የውሻ ሽንት ብረት መቦርቦር ይችላል

በውሻዎች ሽንት ውስጥ የሚገኘው አሲድ ብረት የመቦርቦር ሀይል እነዳለው ነው የሚነገረው።

3. ውሻዎች ቀለም መለየት ይችላሉ

በአፈ ታሪክ ውሻዎች ነጭ እና ጥቁር ቀለም ብቻ ነው መለየት የሚችሉት ይባላል።

ይሁን እንጂ እንደ ሰዎች ሁሉ ውሻዎችም ቀለማትን በደምብ መለየት እንደሚችሉ በጥናት ተረጋግጧል። ውሻዎች በሰማያዊ እና ቢጫ ስኬል ቀለማትን መለየት የሚችሉ ሲሆን፥ በቀይ እና አረንጓዴ ስኬል ግን ቀለማትን መለየት አይችሉም።

ውሻዎች ከሰዎች በተሻለ በምሽት የማየት ችሎታ አላቸው።

4. በሽታን ማሽተት ይችላሉ

በጀርመን ስቺለርሆል ሆስፒታል የተደረገ ምርምር ውሻዎች የሰው ልጆች የሰውነት ክፍሎች ስራቸውን በአግባቡ እየከወኑ አለመሆኑን የሚጠቁሙ ኦርጋኒክ ውህዶችን ማሽተት እንደሚችሉ አሳይቷል።

ውሻዎች ለካንሰር የተጋለጡ ሰዎችን በማሽተት ማወቅ እንደሚችሉ የተነገረ ሲሆን፥ ይህ የሆስፒታሉ ግኝት ግን በቀጣይ ሰፊ ጥናት ይፈልጋሉ ተብሏል።

5. ብልጣ ብልጥ ናቸው

በአሜሪካ የስነ ልቦና ማህበር አደረግኩት ባለው ጥናት ውሻዎች ከሁለት አመት ህፃን ልጅ የበለጠ አስተሳሰብ እንዳላቸው ደርሼበታለሁ ብሏል።

ቦርደር ኮሊስ የተባለው ውሻ ከ200 በላይ ቃላትን መረዳቱ የውሻዎችን የአዕምሮ ብቃት ያሳየ መሆኑ ተጠቁሟል።

6. ጭራቸውን ማወዛወዛቸው ሁሌም የደስታቸው ምልክት አይደለም

ውሻዎች ጭራቸውን ሲያወዛውዙ ራሱን የቻለ ትርጉም አለው። ወደ ቀኝ ሲያወዛውዙ መደሰታቸውን፤ ወደ ግራ ሲያወዛውዙ ደግሞ ፍርሃት እንደተሰማቸው ይገልፃሉ።

7. ከሰዎች የበለጠ የሰውነት ሙቀት አላቸው

የሰው ልጅ መደበኛ የሰውነት ሙቀት 37 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሲሆን፥ የውሻዎች ግን ከ38 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ ነው።

ለዚያም ነቅ ቁንጫዎች ከሰዎች ይልቅ በውሻ ፀጉር መሰግሰግን የሚመርጡት።

8. ህልም ያልማሉ

በእንቅልፍ ልባቸው ሲንቀሳቀሱ እና ሲያንሾካሹኩ ለሚያዳምጥ ሰው ውሻዎች እንደ ሰው ልጅ ሁሉ ህልም ያልማሉ ቢሉት ለማመን አይከብደውም።

ይሁን እንጂ ሁሉም ውሻዎች እኩል ህልም አያዩም።

ትንንሽ ወሻዎች ከትልልቅ ውሻዎች ይልቅ ብዙ ህልም ያያሉ።

9. በፍቅር ይወድቃሉ

በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ፖል ዛክ፥ የውሻዎች አዕምሮ ኦክይቶሲን የተሰኘ የፍቅር ሆርሞን እንደሚለቅ አረጋግጫለሁ ብለዋል።

ውሻዎች ከሰዎች እና ከመሰሎቻቸው ጋር ሲገናኙ አዕምሯቸው የሚለቀው ሆርሞን የሰዎች አዕምሮ በመተቃቀፍ እና መሳሳም ጊዜ ከሚለቀው ሆርሞን ጋር ተመሳሳይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

10. ሰዎች ለምን ውሻዎችን አጥብቀው ወደዱ?

ተመራማሪዎች እንደሚሉት ሰዎች እና ውሻዎች ጓደኝነት መመስረት የጀመሩት ከ30 ሺህ አመት በፊት ነው።

ጥብቅ ግንኙነታችን የጀመረው በአውሮፓ የበረዶ ዘመን በአደን ኑሯቸውን የሚገፉ ሰዎች ተኩላዎችን ማላመድ ሲጀምሩ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

 

 

ምንጭ፦ www.mirror.co.uk

 

 

በፋሲካው ታደሰ