በአየር ብክለት የተቸገሩት ቻይናውያን ንጹህ አየር ፍለጋ ገበያ ወጥተዋል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በተበከለ አየር የተቸገሩት የቻይናዋ ዢያን ከተማ ነዋሪዎች ንጹህ አየርን ገበያ ወጥተው ነው የሚገዙት።

የቀድሞ የቻይና ዋና ከተማ በሆነችው ዢያን የሚኖሩ ሰዎች 18 ዩዋን እጃቸው ላይ ከያዙ በቀጥታ የሚያደርጉት ለ2 ደቂቃ የሚተነፍሱትን ንጹህ አየር መግዛት ነው።

fresh_air.jpg

ንጹህ አየሩ ኪንሊንግ ከተባለ ተራራ ላይ የሚመጣ ሲሆን፥ ተራራው በመካከለኛው የቻይና ክፍል ነው የሚገኘው።

3 ሺህ 771 ሜትር ከፍታ ያለው ይህ ተራራ ሀገሪቱን በሰሜን እና በምእራብ በኩል ለሁለት ከፍሎ ነው የሚታየው።

የተራራው 94 በመቶም በአረንጓዴ ደን የተሸፈነ ነው።

ታዲያ ዢያን ከተማ የደን ቢሮ ከዚህ ተራራ ላይ ንጹህ አየርን በማምጣት ለህብረተሰቡ የመሸጥ ሀሳብን ከአንድ ዓመት በፊት ነበር ይዞ የመጣው።

ይህ ሀሳብ የመጣውም የዢያን ከተማ ከዓመት በፊት በተበለከ አየር ጉም በተሸፈነችበት ወቅት ነው።

የከተማዋ አስተዳደርም ይህን ፕሮጀክት እውን ለማድረግ 200 ሺህ የቻይና መገበያያ ገንዘብ (ዩዋን) ወጪ ማድረጉ ነው የተገለፀው።

በአሁኑ ጊዜም የንጹህ አየር ገበያው በዢያን ከተማ የደራ ሲሆን፥ አንዱ እሽግ ንጹህ አየርም በ60 የቻይና ዩዋን በመሸጥ ላይ ይገኛል።

fresh_arir.jpg

ስፍራው ድረስ በመሄድ የሚጎበኙ ሰዎች ግን ለሁለት ደቂቃ የሚተነፍሱትን ንጹህ አየር በ18 የቻይና ዩዋን በመግዛት እየተጠቀሙ መሆኑም ታውቋል።

ምንጭ፦ CGTN