የ7 አመቱ ህፃን ቆሻሻን ወደ ሀብትነት በመቀየር ተጠምዷል

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ኦሬንጅ ካውንቲ ነዋሪ የሆነው የሰባት አመት ህፃን የመቦረቂያ ጊዜውን በበጎ ተግባር እያሳለፈ ነው።

ሪያን ሂክማን የተባለው ህፃን ቆሻሻን ወደ ሀብት በመቀየር ላይ ይገኛል ተብሏል።

ህፃኑ ስራ ፈጣሪ በሶስት አመቱ በመኖሪያ አካባቢያቸው የሚገኝ የቆሻሻ በድጋሚ ጥቅም ላይ ማዋያ ማዕከልን ከአባቱ ጋር ከጎበኘ በኋላ ነው ይህን ቢዝነስ ለምን እኔስ አልሰማራበትን የሚል ሀሳብ ያቃጨለበት።

የሪያን አባት ዳሚዮን ሂክማን ካፒስትራኖ ለተባለ ጋዜጣ እንደተናገሩት፥ ህፃኑ ማዕከሉን በጎበኘ ማግስት ከቤት እና ከጎረቤት ጥቅም ላይ ውለው የሚጣሉ ፕላስቲክ የውሃ ጠርሙሶችን ማሰባሰብ ይጀምራል።

በሂደትም ጓደኞቹ፣ የቤተሰቡ አባላት እና ሌሎች አጋሮቹ ከሪያን ጋር መሰራት መጀመራቸውንም አባቱ ይናገራሉ።

BByaOv9.jpg

ሪያን በሳምንት የተወሰኑ ቀናት የሰበሰባቸውን እቃዎች አጠራቅሞ እንደገና ጥቅመማለይ ወደሚውሉበት ፋብሪካ ይወስዳቸዋል።

ወላጆቹ እንደሚሉት ሪያን ባለፉት ጥቂት አመታት ከ200 ሺህ በላይ የፕላስቲክ ጠርሙሶችን በድጋሚ ጥቅም ላይ እንዲውሉ አድርጓል።

አስተዋዩ ህፃን ከዚህ ቢዝነሱ እስካሁን ከ10 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የቆጠበ ሲሆን፥ ገንዘቡን ለኮሌጅ ትምህርቱ ክፍያ እንደሚያውለው ተናግሯል።

በሚያጠራቅመው ገንዘብ የራሱን የቆሻሻ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ለመግዛት ሊጠቀምበት እንደሚችልም ነው የገለፀው።

ሪያን የተለያዩ ቁሳቁሶችን ከመጣል ይልቅ በድጋሚ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ ሁለት ጥቅሞች አሉት ይላል፤ አንደኛው የአካባቢ ንፅህናን መጠበቅ ነው፤ ሌላኛው ጥቅሙ ደግሞ ገንዘብ ያስገኛል ይላል።

የሪያንን አገልግሎት የሚሹ ሰዎች በድረ ገፅ ቀጠሮ በመያዝ ቆሻሻቸው ይነሳላቸዋል።

የሰባት አመቱ ስራ ፈጣሪ በካሊፎርኒያ ላጉና የባህር ዳርቻ የሚገኘው ፓስፊክ ማሪን ማማል ሴንተር ታዳጊ አምባሳደር ሆኖ ያገለግላል።

ምንጭ፦ www.msn.com/


በፋሲካው ታደሰ