የቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ የግዕዝ ቋንቋ ማስተማር ጀመረ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 3 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ ጥንታዊውን የኢትዮጵያ የግዕዝ ቋንቋን መስጠት ጀመረ፡፡

ዩኒቨርሲቲው ቋንቋውን ለ25 ተማሪዎች በመስጠት ነው ማስተማር የጀመረው፡፡

የዩኒቨርሲቲው የሩቅና መካከለኛው ምስራቅ ስልጣኔዎች ዲፓርትመንት መምህር ፕሮፌሰር ሮበርት ሆልምስቴድ፥ የመጀመሪያውን የግዕዝ ትምህርት መስጠት ጀምረዋል፡፡

የትምህርቱ መጀመር ለዘመናት በቂ ጥናት ሳይደረግበት የቆየውንና በርካታ ፅሁፎች የተፃፉበትን ቋንቋ በማስተማር ታሪክን ለማጥናት እንደሚያስችላል ታምኖበታል፡፡

የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት የሆኑ ተማሪዎች እውቀት ብቻ ሳይሆን ታሪካቸውንና ቋንቋቸውን የሚማሩበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ለትምህርቱ መጀመር በመድረክ ስሙ ዘ ዊኬንድ የሚል መጠሪያ ያለው ትውልደ ኢትዮጵያዊው አቤል ተስፋዬ ድጋፍ አድርጓል፡፡

ከእርሱ በተጨማሪም በካናዳ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት እና የዩኒቨርሲቲው የስነ ጥበብ እና የሳይንስ ትምህርት ክፍልም ድጋፋቸውን አድርገዋል፡፡

የትምህርት ክፍሉ ሃላፊ ፕሮፌሰር ቲም ሃሪሰን ትምህርቱን በሰሜን አሜሪካ የማስፋፋት ሃሳብ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን፣ የመካከለኛውን ዘመን ታሪክ አጥኝዎችና ተመራማሪዎች እንዲሁም የኢትዮጵያን ቋንቋ የማጥናት ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች ትምህርቱን መከታተል ጀምረዋል፡፡

በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ መጽሃፍት የተጻፉበት የግዕዝ ቋንቋ በኢትዮጵያ በአብዛኛው በቤተ ክርስቲያን ብቻ አገልግሎት ላይ ይውላል፡፡


ምንጭ፦ www.utoronto.ca

android_ads__.jpg