17 ጊዜ ፅንስ የተቋረጠባት እንግሊዛዊት በ9 ወራት ውስጥ የ4 ልጆች እናት ሆናለች

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) እንግሊዛዊቷ ሊትና ካዑር ከእንግዲህ መውለድ አትችይም ተብላ የአራት ልጆች እናት ሆናለች።

በጎርጎሮሳውያኑ 2007 ሰርጓን ካደረገች በኋላ ልጅ ወልዳ ለመሳም ጉጉት ያደረባት ሊትና ልጅ አልሆንሽ ይላታል።

ሊትና ቀይ የደም ህዋስን በመጉዳት በአጥንት ውስጥ የነጭ የደም ሴል ካንሰርን በሚያመጣ በሽታ በመጠቃቷ ምክንያት መውለድ እንደማትችል በሃኪሟ ይነገራታል።

በእንግሊዝ ኖቲንግሃም ወላቶን የምትኖረው የ32 ዓመቷ ሊትና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለዓመታት 17 ያልፈለገቺው የወሊድ ማቋረጥ (የፅንስ መጨናገፍ) እንዳጋጠማት ትናገራለች።

"17 ጊዜ ፅንስ ተቋርጦብኛል፤ ሁሉም ከባድ ነበሩ በተለይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጨናገፈብኝ ፅንስ በጣም ከባድ ነበር፤ ያረገዝኩት ሁለት ፅንስ ስለነበር እና ረዥም የእርግዝና ወራትን በመግፋቴ ፅንሶቹ ሲቋረጡ አካላዊ እና አዕምሯዊ ጉዳቱ ከባድ ነበር" ብላለች፡፡

በ2010 ፀንሳ ከተጨናገፈባት በኋላ ልጅ ለመውለድ ያልቻለቺው እና በዚህ የተማረረቺው ሊትና፥ የጉዲፈቻ ልጆችን ለማሳደግ ብታፈላልግም የሚሆናትን ልጅ በእስያ ምድር አላገኘሁም ትላለች፡፡

ይህን ተከትሎም ሊትና እና ባለቤቷ ማህፀኗን ለፅንሳቸው የምታከራያቸውን ሴት መፈለግ ጀመሩ።

ከ2013-2015 ባለው ጊዜ ውስጥ በህንድ የሚገኝ አንድ ሆስፒታል ስድስት ጊዜ የሊትና እና ባለቤቷን የዘር ፍሬ በሌሎች ሴቶች ማህን ለማሳደግ ቢሞክርም አራቱ ሳይሳኩ ቀርተዋል፡፡

ግራ የገባቸው ሊትና እና ባለቤቷ ቀን ሄዶ ቀን ሲመጣ በ2015 የካቲት ወር ላይ ሊትና በተፈጥሯዊ መንገድ መፀነሷን ያውቃሉ፡፡

ከዚህ በፊት በነበራት መጥፎ ኣጋጣሚ ምክንያት እርግዝናው ይቋረጥብኛል በሚል ፍራቻ ውስጥ ትገባለች - ሊትና፡፡

ቀናት ተደማምረው ወራትን ሲተኩ ተስፋ ያልቆረጠቺው ሊትና፥ በመስከረም ወር 2015 የፈረንጆች ዓመት ኪራን የተባለች ሴት ልጅን በኩዊን የህክምና ማዕከል በተደረገላት የቆዶ ጥገና ህክምና አማካኝነት ተገላግላ አይኗን በአይኗ አየች።

17_women3.jpg

በዚያው ዓመት ህዳር ወር ላይም በህንድ በሚገኝ ሆስፒታል የሊትና እና ባለቤቷ የዘር ፍሬ በሌላ ሴት ማህፀን ውስጥ እንዲያድግ ተደርጎ ካጃል እና ካቪታ የተባሉ መንታ ሴት ህጻናት እርሷ ባትወልዳቸውም ፅንሱ የተገኘው ከእርሷ እና ከባለቤቷ የዘር ፍሬ በመሆኑ የሶስት ልጆች እናት ሆነች፡፡

ከአንድ ወር በኋላ ሊትና ወደ ህንድ አምርታ መንትያ ልጆቿን ወደ ኖቲንግሃም ለማምጣት በሄደችበት ጊዜም በሆዷ ፅንስ መኖሩ ወይም በተፈጥሯዊ መንገድ ማርገዟ ተረጋገጠ።

በፈረንጆች 2016 ሰኔ ወር ላይ ኪያራ የተባለች ሴት ልጅም ወልዳ ሳመች፡፡

በወራት ውስጥ የአራት ሴት ልጆች እናት የሆነቺው ሊቲና በጤናዋ ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ተናግራለች።

17_women2.jpg

"በዕውነት እኔ እና ባለቤቴ እድለኞች ነን" ስትልም ተደምጣለች፡፡

"በዘጠኝ ወር ውስጥ ያልጠበኩት ነገር መከሰቱ በእውነት አስገርሞኛል፤ እናትነቱም ተስማምቶኛል" ነው ያለቺው ሊትና።

 

ምንጭ፡- www.dailymail.co.uk/


በምህረት አንዱዓለም