በባለቤቱ የቀብር ስነ ስርዓት ላይ ሲያለቅስ የታየው ፈረስ የበርካቶችን ልብ ሰብሯል

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 28፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በብራዚል የባለቤቱን ሞት ያወቀው ፈረስ በቀብሩ ላይ ተገኝቶ ማልቀሱ የብዙዎችን ልብ ነክቷል፡፡

የ34 ዓመቱ ብራዚላዊው ዋግነር ዲልማ ፊጉዌሪዶ እና ሰሬኖ የተሰኘው ፈረሱ ጥብቅ የሆነ ግንኙነት፣ በታማኝነት እና በፍቅር የተሞላ ጓደኝነት ነበራቸው፡፡

ዋግነር ነጩን ፈረሱን ሰሬኖ በመጋለብ ላለፉት ስምንት ዓመታት በፈረስ ስፖርቶች በርካታ ትርኢቶችን ለህዝብ አሳይቷል፡፡

በሰሬኖ በርካታ ውድድሮችን ያሸነፈው ዋግነር የገንዘብ እና ሌሎች ሽልማቶችን አግኝቷል፡፡

horse_1.jpg

የሆነው ሆኖ በጎርጎሮሳውያን የ2017 አዲስ ዓመት የሰሬኖ ባለቤት ዋግነር፥ በሚኖርባት ከተማ የባህር ዳርቻ ሞተር ሳይክል ሲነዳ ሚዛኑን በመሳቱ አደጋ ይደርስበታል፡፡

ይህን ተከትሎም በአካባቢው ባሉ የጤና ተቋማት የቀዶ ህክምናዎች ቢደረጉለትም የዋግነር ነፍስ ከስጋዋ ተለይታለች፡፡

ሰሬኖም የባለቤቱን መሞት እንዳወቀ እና አስከሬኑ ከቤት ወደ መቃብር ቦታ ሲሄድ ድምጽ አውጥቶ ተንሰቅስቆ ሲያልቅስ ታይቷል፡፡

bro_horse.jpg

ሰሬኖ በሟች ወንድም በዋንዶ ዲልማ አማካይነት ማክሰኞ እለት በሰሜን ምስራቋ ብራዚል ፓራኢባ ግዛት ተገኝቶ፥ በአሳዛኝ ስሜት ውስጥ ሆኖ በእግሩ መሬቱን እየደበደበ ድምጽ አውጥቶ በማልቀስ እርሙን አውጥቷል።

የዋግነር ወንድም ዋንዶ ዲልማ እንዲህ አለ፤ "ይህ ፈረስ ለወንድሜ ሁሉ ነገሩ ነበር፤ ሆኖም ያልተጠበቀው እና የማይቀረው ሞት ወንድሜን ወስዶታል፤ ፈረሱ ሰሬኖም ይህን በማወቁ ደህና ሁን ለማለት ተገዷል" ብሏል

የዋግነር ቤተሰቦች እና ሀዘንተኛ ጓደኞች በ34 ዓመቱ ዋግነር የቀብር ስነስርዓት በተገኙበት ወቅት የሟች ንብረት የሆነው ሰሬኖ በአስከሬኑ ላይ ጭንቅላቱን እያወዛወዘ በሀዘን ገጽታ ታይቷል፡፡

horse_hazne.jpg

ይህን ክስተት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በአግራሞት እና ባለማመን የተመለከቱት ሲሆን በየመንደሩ እና በየማህበራዊ ሚዲያው መነጋገሪያ ሆኗል፡፡

horse2.jpg

በባለቤቱ የቀብር ስነስርዓት የሰሬኖን የተጨነቀች መንፈስ እና የሀዘን ገፅታ ማየት ልብን ይሰብራል ነው ያሉት በቀብሩ ላይ ታድመው የነበሩ ሰዎች፡፡

"የዋግነር ህይወት ፈረሱ ነበር፤ በመካከላቸው ትልቅ ፍቅር ነበር፤ ዋግነር ለራሱ የሆነ ነገር ከሚገዛ ይልቅ ለፈረሱ ምግቦችን መግዛት ያስደስተዋል፤ ነጩን ሰሬኖን ለመግዛት በርካታዎች ጥያቄ ቢያቀርቡለትም ለመሸጥ ፈቃደኛ አልነበርም" ነው ያለው የሟች ወንድም ዋንዶ ዲልማ፡፡

bro_horse.jpg

በብራዚል የፈረስ ግልቢያ ፌዴሬሽን ላለፉት 20 ዓመታት የእንስሳት ሃኪም ሆነው የሚያገለግሉት ማርሴሎ ሰርቮስ፥ “ፈረሶች የባለቤታቸውን ወይም የሚወዱትን ሰው ሞት የሚያውቁ ሲሆን በሞቱም ያዝናሉ" ነው ያሉት፡፡

ምንጭ፦ www.dailymail.co.uk

ተተርጉሞ የተጫነው፦ በምህረት አንዱአለም

android_ads__.jpg