የሰኔ ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 14 ነጥብ 7 በመቶ ሆኖ ተመዘገበ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ፣ 28፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሰኔ ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 14 ነጥብ 7 በመቶ ሆኖ መመዝገቡን የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ መሰረት የዋጋ ግሽበቱ ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር የ1 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

የሰኔ ወር ምግብ ዋጋ ግሽበት 17 ነጥብ 9 በመቶ ሆኖ ሲመዘገብ፤ ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ዋጋ ደግሞ ወደ 11 ነጥብ 1 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል።

ካለፈው ወር ጋር ሲነጻጸር በያዝነው ወር ዳቦና የእህል ክፍሎች፣ ሥጋ፣ ቅቤ፣ ወተት፣ አይብና ዕንቁላል ላይ ጭማሪ ታይቷል።

በተጨማሪም አትከልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የቅመማ ቅመም ዋጋ ላይ ጭማሪ መታየቱ የዋጋ ግሽበቱ ከፍ እንዲል ካደረጉ ምክንያቶች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው።

ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ደግሞ አልባሳትና ጫማ፣ የቤት ማደሻ እና ማስዋቢያ ቁሳቁሶች፣ የሀይል ፍጆታዎች እንዲሁም በሆቴሎች የሚወሰዱ ምግቦችና መጠጦች ላይ ጭማሪ ታይቷል።

በተጨማሪም በትራንስፖርት እና በህክምና ወጪዎች ላይ ጭማሪ መታየቱን የዋጋ ግሽበቱ ከፍ እንዲል ካደረጉ ምክንያቶች ውስጥ መሆኑን ኤጀንሲው አስታውቋል።