ከቅመማ ቅመም ዘርፍ የሚገኘው ገቢ በአማካይ በዓመት ከ21 ሚሊየን ዶላር አይበልጥም

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 6 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እምቅ የቅመማ ቅመም ሀብት ባለቤት ብትሆንም ከዘርፉ የምታገኘው ገቢ ግን በአማካይ በዓመት ከ21 ሚሊየን ዶላር አይበልጥም።

በአለም ላይ በእጽዋት ደረጃ 109 አይነት፥ በተቀነባበረ ምርት ደረጃ ደግሞ 600 አይነት የቅመማ ቅመም ምርቶች ይገኛሉ።

ከእነዚህ ውስጥ ኢትዮጵያ ለምርቱ ምቹ ከመሆኗ አንጻር እንዲሁም ባላት ለግብርና ተስማሚ የሆነ የአየር ንብረት 63 አይነት የቅመማ ቅመም እጽዋትን ማምረት ትችላለች።

ሆኖም አሁን ላይ እንደሀገር እየተመረቱ ያሉት ግን ከ23 የማይበልጡ ሲሆን፥ ስድስት የቅመማ ቅመም አይነቶችን ደግሞ ወደ ውጭ ለመላክ እቅድ ተይዟል።

እንደ ህንድ ባሉ ሀገራት በአንድ ኩባንያ ደረጃ እስከ 240 ሚሊየን ዶላር አመታዊ ገቢ ሲገኝ፥ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የምታገኘው ገቢ ግን በአማካይ ከ21 ሚሊየን ዶላር ሊበልጥ አልቻለም።

የኢትዮጵያ እና ሆላንድ የንግድ ትብብር ለእድገት ፕሮጀክት የቅመማ ቅመም እና ሀመልማሏማ ምርቶች ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አዲሱ አለማየሁ፥ ለገቢው መቀነስ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ይጠቅሳሉ።

ምርቱ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ኖሮት ሳለ ዋና ዋና ቅመማ ቅመም አምራች በሆኑ ክልሎች እስካሁን እስከ አርሶ አደሩ የሚደርስ መዋቅር እና አደረጃጀት አለመኖሩን በዋናነት ያነሳሉ።

ከዚህ ባለፈም ቅመማ ቅመም አምራች ገበሬው በቴክኖሎጅ እና በምርጥ ዘር አቅርቦት እየተደገፈ አለመሆኑን ጠቅሰው፥ የቅመማ ቅመም ምርጥ ዘር እና ፀረ ተባይ አቅራቢ ተቋም እንደሌለም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ለምርት ጥራት መጓደል ምክንያት የሆነው የአፍላ ቶክሲን እንዲሁም በግብይት ሂደቱ የህገ ወጥ ደላሎች መበራከት እና የገበያ ማጭበርበር ለዚህ ተጠቃሽ መሆናቸውን አቶ አዲሱ ተናግረዋል።

በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ ቅመማ ቅመም መዳረሻ ለምርት ጥራት ክብደት ከማይሰጡት ጎረቤት ሀገራት ሱዳን፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ መሻገር አልቻለም ነው ያሉት።

አሁን ላይም በቅመማ ቅመም ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ሊፈቱ የሚችሉ ስራዎችን፥ በቴክኖሎጅ እና ንድፈ ሀሳብ አዲስ የፈጠራ ሀሳብ ያላቸውን ሰዎች በገንዘብ በመደገፍ መሰራት መጀመሩንም ነው የተናገሩት።

ከዚህ ባሻገር ግን መንግስት እና ባለድርሻ አካላት በተለይም የቅመማ ቅመም ምርት በግብርና ኤክስቴንሽን ስርአት እንዲደገፍ ሊሰሩ እንደሚገባም ይጠቅሳሉ።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በበኩሉ ለዘርፉ አለማደግም ሆነ ለተጠቀሱት ችግሮች መነሻው ለምርቱ የተሰጠው ዝቅተኛ ግምት ነው ይላል።

የባለስልጣኑ የቅመማ ቅመም ሰብሎች ኤክስቴንሽን ቡድን መሪ ወይዘሮ ገነት ቱፋ እንዳሉት፥ ዘርፉ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል የሚፈጥር እና ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ቢኖረውም ትኩረት ተነፍጎታል።

ከምርጥ ዘር እና ግብአት አቅርቦት ጋር በተያያዘ የሚታየው ችግር ግን በመንግስት በተቋቋመሙ የምርምር ማዕከላት በሚጠበቀው ልከ ዘርፉን ባለመደገፋቸው የተፈጠረ መሆኑንም አስረድተዋል።

ከዚህ ባለፈም ባለሀብቱ በልማቱ እንዲሳተፍ በማድረግ በኩል ክፍተት መኖሩን ጠቅሰው፥ ባለስልጣኑም ባለሃብቱን ለመሳብ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በአጠቃላይ የቅመማ ቅመም ዘርፉን ለማሳደግ ባለስልጣኑ በቡድን ደረጃ ያለውን አደረጃጀት ወደ ዳይሬክተር ደረጃ በማሳደግ ስራዎችን በስፋት ለመስራት ማሰቡንም ጠቁመዋል።

ባለፉት 10 ወራት ወደ ውጭ ከተላከ የቅመማ ቅመም ምርት 9 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር ብቻ መገኘቱን ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

 

 

 

በቤተልሄም ጥጋቡ