ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከተጠየቀው የማሽነሪ ግዥ 20 በመቶው ብቻ ተፈጽሟል

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 1 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በበጀት አመቱ ዘጠኝ ወራት የ10 ቢሊየን ብር የማሽነሪ ሊዝ ፋይናንስ ጥያቄ ቢቀርብም አፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆኑን የፌደራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱትስሪ ይገልጻል።

መንግስት በማምረቻው ዘርፍ መሰማራት ለሚፈልጉ ግለሰቦችም ሆኑ ማህበራት የማሸኑን 20 በመቶ በማስያዝ እና አዋጭ የሆነ ንድፈ ሀሳብ በማቅረብ በማሽነሪ ሊዝ ፋይናንስ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሁኔታዎችን አመቻችቷል።

ይህንኑ የመንግስት እቅድ ለመደገፍም የአለም ባንክ እና የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ለአምስት አመት የሚቆይ 276 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ፕሮጀክት በዚህ አመት ይፋ አድርገዋል።

የፌደራል አነስተኛ እና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲ በበኩሉ፥ በበጀት አመቱ ዘጠኝ ወራት በማሸነሪ ሊዝ ፋይናንስ ተጠቃሚ ለመሆን በርካታ ጥያቄዎች ማስተናገዱን ገልጿል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ በበጀት አመቱ ዘጠኝ ወራት ከተጠየቀው 10 ቢሊየን ብር ዋጋ ካለው የማሽነሪ ግዥ ማከናወን የተቻለው 20 በመቶ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ እድል ተጠቃሚ መሆን የሚፈልግ አካል ከ5 መቶ ሺህ እስከ 7 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገበ፣ ትኩረት በተሰጣቸው የማምረቻ ዘርፎች ላይ አዋጭ ንድፈ ሀሳብ ያቀረበ፣ ህጋዊ ፍቃድና የማምረቻ ቦታ እና የማሽነሪውን 20 በመቶ ማስያዝ ይጠበቅበታል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በበኩሉ ለአምስት አመት የሚቆይ እና ለማምረቻው ዘርፍ የሚውል በአለም ባንክ እና በአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ድጋፍ ከተደረገው 276 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ፕሮጀክት ውስጥ 60 ሚሊየን ዶላሩ መለቀቁን ገልጿል።

የባንኩ የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ፋይናንሲንግ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተሾመ አለማየሁ፥ ገንዘቡ ተለቆ እየተሰራ ቢሆንም ተገልጋዩን በሚፈለገው ደረጃ ከማስተናገድ አኳያ የተነሳው ውስንነት ትክክል መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለዚህም ስራው አዲስ ከመሆኑ አንጻርና የማሽነሪዎቹ ግዥ ጊዜ መውሰዱን በምክንያትነት አንስተዋል።

በባንኩ በኩል እስከ ሚያዚያ ወር ማብቂያ ድረስ ከ872 ሚሊየን 841 ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ፥ የ223 ፕሮጀክቶች ማሽነሪ ግዥ እና የተከላ ስራ ተጠናቆ ስራ ወደ ስራ ገብተዋል።

2 ቢሊየን 678 ሚሊየን ብር በላይ ካፒታል የሚጠይቁ 361 ፕሮጀክቶችም የስራ ንድፈ ሀሳባቸው ተገምግሞ የፀደቀ ሲሆን፥ ከ948 ሚሊየን ብር በላይ የሚሆነው ማሽነሪ ደግሞ በግዥ ሂደት ላይ ይገኛል ነው የተባለው።

ይህ አሃዝ ግን ካለው ፍላጎት አንጻር ሲገመገም ዝቅተኛ መሆኑን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

አሁን ላይ ከማሽነሪ ግዥ እና አቅርቦት ጋር በተያያዘ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፥ አዳዲስ ቅርንጫፎች መከፈታቸውን ጠቁመዋል።

ወደ ስራ የገቡትን ለማበረታታትም ሆነ ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግም፥ የግብይቱ ተዋንያን ለሀገራቸው ምርት ቅድሚያ በመስጠት ዘርፉን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ማገዝ ይገባቸዋል ነው የተባለው።

 

 


በሰርካለም ጌታቸው