ባለፉት 10 ወራት ከወጪ ንግድ 2 ነጥብ 35 ቢሊየን ዶላር ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በበጀት ዓመቱ ባለፉት 10 ወራት ከወጪ ንግድ 2 ነጥብ 35 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን የንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በአስር ወራቱ ከወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 64 ነጥብ 51 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ጭማሪ ማሳየቱንም ሚኒስቴሩ ገልጿል።

እንደ ሚኒስቴሩ ገለፃ ባለፉት 10 ወራት ከግብርና ምርቶች ዘርፍ 1 ነጥብ 79 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የተገኘ ሲሆን፥ ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ61 ነጥብ 17 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ጭማሪ አሳይቷል።

በተመሳሳይ ከማምረቻው ዘርፍ 371 ነጥብ 34 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን፥ ይህ አፈፃፀም ከአምናው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወራት ጋር ሲነፃፀር በ 50 ነጥብ 5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ጭማሪ ማሳየቱም ተገልጿል።

ከማዕድን ዘርፍ ደግሞ ባለፉት 10 ወራት የተገኘው ገቢ 115 ነጥብ 35 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር መሆኑንም የንግድ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ገቢው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው ገቢ ጋር ሲነፃፀር በ 51 ነጥብ 9 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ቅናሽ አሳይቷል ነው ያለው ሚኒስቴሩ።