ሀገሪቱን ከጎበኙ ቱሪስቶች ከ2 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

አዲስአባባ፣ ግንቦት 3 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከጎበኟት ቱሪስቶች 2 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር ማግኘቷን እና ይህም የእቅዱ 75 በመቶ እንደሆነ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለፀ።

1 ነጥብ 2 ሚሊየን ቱሪስቶች በዘጠኝ ወራት ውስጥ ሀገሪቷን ይጎበኛሉ ተብሎ ቢታቀድም 756 ሺህ 758 ቱሪስቶች እንደጎበኟች ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።

ከዕቅዱ አንጻር ውጤቱ አመርቂ እንዳልሆነ እና ባለፉት ጊዜያት በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የነበረው የፀጥታ ችግር አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደሩን በሚኒስቴሩ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ገዛኽኝ አባተ ተናግረዋል።

ለተከታታይ ሶስት ዓመታት የጎብኚዎችን ቁጥር አንድ ሚሊየን ለማድረስ ቢታቀድም በተለያዩ ምክንያቶች እቅዱ ግቡን ሊመታ እንዳልቻለም ገልፀዋል።

በባህል ልማት እና በመስህብ መዳረሻዎች ላይ የሚሰሩ ስራዎች አጥጋቢ አለመሆናቸው የፈጠሩት ክፍተት፥ ሃገሪቱ ከቱሪዝም ዘርፉ እንዳትጠቀም እንዳደረጋት ይነገራል።

የቱሪዝሙን ዘርፍ ለማሳደግ መሰረት ልማቶችን፣ ሆቴሎችን እና ሌሎች አገልግሎቶችን እና መሰረተ ልማትን ማስፋፋት ዘርፉን ይበልጥ ለማሳደግ አስፈላጊ እንደሆኑ ተጠቁሟል።

የበጀት አመቱ ሲጠናቀቅ ከቱሪዝም ዘርፉ 4 ነጥብ 5 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት እንደታቀደ ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት።

ምንጭ፦ ኢዜአ