ምርት ገበያው በሚያዚያ ወር የ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ምርት አገበያየ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በሚያዚያ ወር 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ዋጋ ያለው ምርት ማገበያየቱን አስታወቀ።

ምርት ገበያው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፥ በሚያዚያ ወር ያገበያየው አጠቃላይ የምርት መጠን 45 ሺህ ቶን ነው።

በወሩ የቡና ግብይት ከፍተኛውን ድርሻ መያዙን የጠቀሰው ምርት ገበያው፥ 30 ሺህ ቶን ቡና በ2 ቢሊየን ብር ማገበያየቱን ገልጿል።

በተጨማሪም 11 ሺህ ቶን ሰሊጥ በ426 ሚሊየን ብር፣ 3 ሺህ 95 ቶን ቦሎቄ በ46 ሚሊየን ብር እንዲሁም 1 ሺህ 377 ቶን አረንጓዴ ማሾ በ27 ሚሊየን ብር አገበያይቷል።

የሚያዚያ ወር የቡና ግብይት ከመጋቢት ወር ጋር ሲነፃፀር በመጠንና በዋጋ የ18 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።

የቡና ግብይቱ ከአጠቃላይ ግብይቱ በመጠን 66 በመቶና 81 በመቶ በዋጋ እንደያዘም ተገልጿል።

የሰሊጥ ግብይት በዋጋ ደረጃ ከቡና ቀጥሎ ገቢ ቢያስገባም በመጠንም ሆነ በዋጋ ከፍተኛ ቅናሽ አሳይቷል ነው የተባለው።

ምርት ገበያው በመግለጫው ከነገ ግንቦት 4 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ የግብይት ክፍያ አገልግሎቱን ከመደበኛ የስራ ቀናት በተጨማሪ ዘወትር ቅዳሜ እንደሚሰጥ አስታውቋል።