በመዲናዋ የመሰረታዊ ሸቀጦች በኩፖን እንዲሆን ቢደረግም የሚፈልጉትን እያገኙ አለመሆኑን ነዋሪዎች ገለጹ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 3 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የመሰረታዊ ሸቀጦች በኩፖን እንዲሆን ቢደረግም በተሰጣቸው ካርድ የሚፈልጉትን ዘይትም ሆነ ስኳር እያገኙ አለመሆኑን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በመሰረታዊ ሸቀጦች ላይ ፍትሃዊ ስርጭት እንዲኖር በሚል መሰረታዊ የስርጭት ካርድ ወይም ኩፖንን አገልግሎት ላይ ማዋል ከጀመረ ሁለት አመት ሊሞላው ነው።

አሰራሩ በተወሰነ ደረጃ ፍትሃዊነት ቢያመጣም አሁንም የተለያዩ ችግሮች እንዳሉበት ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።

ከዚህ ውስጥ በቢሮው የተመረጡት የማሰራጫ ሱቆች ለህብረተሰቡ ከማከፋፈል ይልቅ ለነጋዴዎች መሸጣቸው በዋናነት የሚስተዋል ችግር መሆኑን ይገልጻሉ።

ባለሱቆቹም ሆኑ በሸማች ማህበራት ውስጥ የሚሰሩ ግለሰቦች በተሰጣችው ሀላፊነት ለሁሉም እኩል መስተንግዶ ከማድረግ ይልቅ፥ ያለውን ዘይትም ሆነ ስኳር ለሚያውቁት ሰው የማስቀመጥና የመሸጥ አድሏዊ አሰራር ይስተዋላልም ነው የሚሉት ነዋሪዎቹ።

በሱቆችም ሆነ በሸማች ማህበራት የተመዘገቡ ሰዎችን ብዛት ያላገናዘበ አቅርቦት በመኖሩ ምክንያት የሚፈጠር እጥረትም ሌላው የችግሩ መንስኤ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህም ቀድመው ወደ ሱቆች የሄዱ ሰዎች የፈለጉትን ምርት ሲያገኙ ቀሪዎቹ ግን አልቋል በሚል ባዶ እጃቸውን ለመመለስ ይገደዳሉም ነው ያሉት።

ችግሩ መኖሩን የሚያምነው የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በበኩሉ ህገ ወጥነቱን ለመከላከል እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ገልጿል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ፍትሃዊ ስርጭቱን አዛብተዋል በተባሉ 545 ድርጅቶች ላይ እንደ ጥፋት ደረጃቸው እና አይነት እርምጃ መውሰዱንም ነው የገለጸው።

በቢሮው የክስ ምርመራና ትስስር ቡድን መሪ አቶ ሃብታሙ ጥላየ እንዳሉት፥ 545 ድርጅቶች ላይ ከስርጭት የማስወጣትና የማሸግ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።

ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ ሱቃቸው እንዲታሸግ የተደረገ ሲሆን፥ 122 የሚሆኑትን ደግሞ ከስርጭት በማስወጣት በሸቀጥ አቅርቦት ላይ እንዳይሳተፉ መደረጋቸውንም ነው የተናገሩት።

አቶ ሃብታሙ እርምጃው ከንግድ ሱቆች በተጨማሪ በዱቄት ፋብሪካዎችና ዳቦ ቤቶች ላይም የተወሰደ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ፋብሪካዎቹ ከዱቄት ጥራት እና የአቅርቦት መጠን ጋር በተያያዘ፥ ዳቦ ቤቶች ደግሞ ከዳቦ ግራም ቅነሳ ጋር ተያይዞ እርምጃ እንደተወሰደባቸውም ገልጸዋል፤ እስካሁን ሶስት ፋብሪካዎች ከትስስሩ እንዲወጡ ተደርገዋል።

ህብረተሰቡ አገልግሎቱን በሚያገኝበት ወቅት የሚያጋጥሙትን ችግሮች በጥቆማ መልክ ቢያቀርብ ቁጥጥሩን ለማጠናከርና አጥፊዎችን በህግ ለመጠየቅ ስለሚረዳ በጥቆማ እንዲተባበር ጠይቀዋል።

ከአቅርቦት እጥረት ጋር በተያያዘም በቀጣይ የኮታ ጭማሪ ለማድረግ ለንግድ ሚኒስቴር ጥያቄ መቅረቡን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

 

 

በትእግስት አብርሃም