በምስራቅ ኢትዮጵያ በኩል ወደ ውጭ ከተላኩ የግብርና ምርቶች 291 ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኘ

አዲስ አባባ፣ ሚያዚያ 30 2010  (ኤፍ.ቢ.ሲ)ባለፉት ዘጠኝ ወራት በምስራቅ ኢትዮጵያ በኩል ወደ ውጭ ከተላኩ የግብርና ምርቶች 291 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ እንደተገኘ ታወቀ፡፡

በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት የተገኘው ይሄ ገቢ 388 ሚሊየን ዶላር ለመሰብሰብ በእቅድ ከተያዘው ውስጥ መሆኑን በንግድ ሚኒስቴር የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ሃድጎ ተናግረዋል ፡፡

ምርቶቹ ወደ ጅቡቲ፣ ሶማሌላንድ ፣ አውሮፓና አሜሪካ የተላኩ ሲሆን፥ ከምርቶቹም መካከል ጫት፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ቡና፣ የቀንድ ከብት፣ ጥራጥሬና የቅባት እህል ናቸው ተብሏል፡፡

ገቢው ከእቅዱ አንፃር በ25 በመቶ እና ከአምናው ተመሣሣይ ወቅት ጋር ደግሞ 12 በመቶ ያነሰ መሆኑ ታውቋል፡፡ 

በተያዘው ዓመት የተከሰተው የፀጥታ ችግር ምርትን በአግባቡ ለመላክ እንቅፋት መፍጠሩና የኮትሮባንድ እንቅስቃሴንም የመከላከሉ ስራ ክፍተት ለገቢው ማነስ በምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡

በአሁን ወቅት የተፈጠረው መረጋጋትና ሰላም በሚቀጥሉት ወራት የተሻለ ሥራ ለማከናወን የሚያስችል በመሆኑ በበጀት ዓመቱ የተያዘው የ400 ሚሊየን ዶላር እቅድ ማሳካት እንደሚቻል አቶ ተስፋዬ አስታውቀዋል፡፡

በውጭም ንግድ እንቅስቃሴው ላይ እንቅፋት እየፈጠረ የሚገኘውን የኮትሮባንድ እንቅስቃሴ የፍትህ አካላትና የምስራቅ ተጎራባች ክፍሎች የፀረ- ኮትሮባንድ ግብረ ሃይል ወጥና ተከታታይ በመሆኑ መንገድ ተቀናጅተው መከላከል ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ምንጭ፦ ኢዜአ