ባንኩ የግምጃ ቤት ሰነድ ግዥው ቅድሚያ ለተሰጣቸው ዘርፎች የሚሰጠው ብድር ላይ ጫና እንደማይፈጥር አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 15 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ቢሊየን ብሮች ዋጋ ያለውን የግምጃ ቤት ሰነድ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ እንደሚገዛ ይናገራል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ መንግስት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ዘርፎች ማለትም እንደ ጨርቃጨርቅ ቆዳ፣ ሰፋፊ እርሻ እና ሌሎች ዘርፎች የሚሰጠውን ብድር፥ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የንግድ ባንኮች በሚሰጡት እያንዳንዱ ብድር ላይ የብድሩን 27 በመቶ ያክል ቦንድ እንዲገዙት በማድረግ ከብሄራዊ ባንክ ያገኛል።

ብሄራዊ ባንክ ለንግድ ባንኮች በዚህ መልኩ ቦንድ ሲሸጥላቸው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ባለው አሰራር በ3 በመቶ ወለድ ሲሆን፥ በዚህ መልኩ ልማት ባንክ ከብሄራዊ ባንክ የሚያገኘውን ገንዘብ መንግስት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ዘርፎች ብድር ያቀርባል።

ሆኖም ከሚሰጠው ብድር ባልተናነሰ ሁኔታ መልሶ ብሄራዊ ባንክ የሚያወጣውን የግምጃ ቤት ሰነድ (ትሬዠሪ ቢል) የሚገዛ ሲሆን፥ ባንኩ በመጽሄቱ ላይ ይፋ እንዳደረገው ባለፈው አመት የገዛው የግምጃ ቤት ሰነድ ዋጋ 13 ነጥብ 65 ቢሊየን ብር ደርሷል።

ይህ ታዲያ ባንኩ በዚህ ሁሉ ቢሊየን ብር የግምጃ ቤት ሰነድ የሚገዛ ከሆነ መንግስት ቅድሚያ ለሰጣቸው ዘርፎች ብድርን እየሰጠ የታለመለትን አላማ እየመታ ነው ወይ የሚል ጥያቄን በባለሙያዎች ዘንድ ያስነሳበታል።

የባንኩ የስትራቴጂ፣ ለውጥና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ክፍሌ ሀይለእየሱስ በበኩላቸው፥ ሁኔታው መንግስት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ዘርፎች ብድር ካለመስጠት አንጻር ሳይሆን ተበዳሪ እስከሚመጣ ሌላ ትርፍ የሚያመጣ ዘርፍ ላይ ገንዘብን ከማፍሰስ አንጻር መታየት አለበት ባይ ናቸው።

ባንኩ በተመሳሳይ አመት የነበረው አጠቃላይ ሀብት 53 ነጥብ 17 ቢሊየን ብር ሲሆን፥ ከዚህ ውስጥ 28 ቢሊየን ብር ሲንከባለል በመጣ ብድር፣ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በንግድ ባንኮች ውስጥ፣ 2 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ደግሞ በውጭ ምንዛሪ ተመንዝሮ በውጭ ባንኮች የተቀመጠ ነው።

ከሀብቱ ውስጥ በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው ደግሞ የ13 ቢሊየን ብር ዋጋ ያለው የግምጃ ቤት ሰነድ ሲሆን፥ ይህን ሰነድ ከብሄራዊ ባንክ በአንድ በመቶ ወለድ ነው የሚያገኘው።

ልማት ባንኩ ለብድር አግኝቶት እንደ አስፈላጊነቱ ለግምጃ ቤት ሰነድ ግዥ የሚያውለው ገንዘብ ከንግድ ባንኮች ሲሰበሰብ ግን የሶስት በመቶ ወለድ ይታሰብበታል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ አካሄዱ ኪሳራ አይደለም ወይ በሚል ለተነሳው ጥያቄ አቶ ክፍሌ በሰጡት ምላሽ፥ የግምጃ ቤት ሰነድ ቢበዛ የስድስት ወራት ያክል እድሜ ያለውና ልማት ባንኩ ተበዳሪ እስከሚመጣ በሌላ ዘርፍ ላይ ሊያውል የሚችለው ሰነዱን በመግዛት መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ አንጻርም የወለዱ ጉዳይ እንደ ችግር የሚነሳ አይደለም ብለዋል።

ባንኩ በአንድ አመት ለተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ሊሰጠው የሚገባውን ከፍተኛ ገንዘብ (13 ቢሊየን ብር) ለግምጃ ቤት ሰነድ አውሎታል፤ ለሰነዱ ይህን ያክል ገንዘብ የሚያውል ከሆነ ልማት ባንኩ በሚገባው ደረጃ ለባለሀብቶች ብድርን እያቀረበ ነው ወይ የሚል ጥያቄ ይነሳል።

የብድር አፈጻጸም ሊገናኝ የሚችለው ከተበዳሪው ቁመና እኔ ሌሎች ጉዳይ ጋር እንጂ ከባንኩ ሰነድ መግዛት ጋር አይደለም ነው የሚሉት አቶ ክፍሌ በምላሻቸው።

የግምጃ ቤት ሰነድን መግዛቱ ከብድር አፈጻጸሙ ጋር ሳይሆን፥ ይህ አይነት ሰነድ ተበዳሪ መረጃ አሟልቶ እስከሚመጣ ለአጭር ጊዜ ገንዘብ የሚፈስበት ኢንቨስትመንት ተደርጎ ሊታይ እንደሚገባውም አስረድተዋል።

 

 


በካሳዬ ወልዴ