በኮምቦልቻና በመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የተሰማሩ ኩባንያዎች ወደ ምርት ሊሸጋገሩ መሆኑን ተናገሩ

አዲስ አበባ ሚያዝያ13፣ 2010(ኤፍ.ቢ.ሲ) በኮምቦልቻና በመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የተሰማሩ ኩባንያዎች ወደ ምርት ለመሸጋገር ዝግጅታቸውን እያጠናቀቁ መሆኑን የውጭ ባለኃብቶች ገለጹ።

በመቀሌና ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የተለያዩ ምርቶችን በማምረት ለውጭ ገበያዎች ለማቅረብ የማምረቻ ማሽኖች ተከላ፣ የሰራተኞች ስልጠና እና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በመስራት ይገኛሉ።

በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ በቆዳ ቦርሳዎች ምርት ለመሰማራት ዝግጅት ላይ የሚገኘው የደቡብ ኮሪያው ፑን ኩክ ኮርፖሬሽን ተወካይ ሚስተር ኦን ሊ እንደተናገሩት ፋብሪካቸው የመሳሪያዎች ተከላና የሰራተኞች ስልጠናን በተያዘው ወር ለማጠናቀቅ እየሰራ ይገኛል።

በአሁኑ ሰዓት ኩባንያው 60 ሰራተኞችን የቀጠረ ሲሆን፥ በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር ከ3 ሺህ በላይ ሊሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራል ተብሏል።

ፋብሪካው ምርቶቹን ወደ አሜሪካ ለመላክ ስምምነት ላይ መድረሱንም ሚስተር ኦን ሊ ተናግረዋል።

ከዚሁ ጎን ለጎን በመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ የተሰማራው የህንዱ ‘የኤስ ሲ ኤም ‘ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ሚስተር ኤ ሽሪኒቫሳን በተመሳሳይ ኩባንያቸው የሰራተኞች ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

ከመጪው ሰኔ ጀምሮ ምርቶቻቸውን ወደ ፈረንሳይ መላክ እንደሚጀምሩና በቀጣይ ወደ አሜሪካና እንግሊዝ ለመላክ ማቀዳቸውንም ተናግረዋል።

ፋብሪካው በሙሉ አቅም ማምረት ሲጀምር በየዕለቱ 40 ሺህ አልባሳቶችን እንደሚያዘጋጅና ለ1 ሺህ 600 ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥርም ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባየሁ እንደገለጹት "በመቀሌና በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኩባንያዎቹ የማሽኖች ተከላ፣የሰራተኞች ቅጥርና ሌሎች ዝግጅቶችን እያከናወኑ ይገኛል።

በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ አለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸው የደቡብ ኮሪያ፣ የቻይና፣የጣሊያንና የአሜሪካ ኩባንያዎች ለመግባት ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን አመላክተዋል።

ኩባንያዎቹ ወደ ስራ ሲገቡ ለ20 ሺህ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ በጨርቃጨርቅና በአልባሳት ዘርፍ የህንድና የባንግላዲሽ ኩባንያዎች የተሰማሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ኩባንያዎቹ ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ሲገቡ ለ30 ሺህ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።
አዳማ፣ድሬዳዋ፣ደብረ ብርሃን፣አረርቲ ፣ባህር ዳርና ጅማ ላይ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እየተከናወነ እንደሚገኝም አቶ አበበ ጠቁመዋል።

የውጭ ባለሃብቶች አዳማ፣አረርቲ፣ድሬዳዋ፣ሞጆ፣አዲስ አበባና መቀሌ ከተሞች የኢንደስትሪ ፓርኮች እየገነቡ ሲሆን፥ ፓርኮቹ ተጠናቀው ወደ ስራ ሲገቡ ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ ስለሚያቀርቡ አገሪቱ በየጊዜው የሚያጋጥሟትን የውጭ ምንዛሬ እጥረት በዘላቂነት ለመፍታት እንደሚያስችል አስረደተዋል።

እንደ አቶ አበበ ገለጻ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በተመረጡ አካባቢዎች መገንባታቸው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር እያደረገ ይገኛል።

የኮምቦልቻና መቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በ190 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተገንብተው በ2009 ክረምት ወራት በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒሰትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መመረቃቸው ይታወቃል።

ኢትዮጵያ የውጭ ባለሃብቶችን በመመልመል፣ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰትን በማሳደግና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው ከፍተኛ የሆኑ ኢንቨስትመንቶችን በማስፋፋት በሚል ከቀናት በፊት በዓለም አቀፉ የኢንቨስትመንት ተቋም የምስራቅ አፍሪካ ተሸላሚ መሆኗ ይታወቃል።

 

 

 

 

ምንጭ፦    ኢ.ዜ.አ