በአፍሪካ ነጻ የጋራ ንግድ ቀጠና ላይ የሚመክር የሚኒስትሮች ጉባኤ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአፍሪካ ነጻ የጋራ ንግድ ቀጠና ላይ ያተኮረ የፋይናንስ፣ የዕቅድና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሮች ጉባኤ በቀጣዩ ወር በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

''የአፍሪካ የጋራ የንግድ ቀጠና ለስራ ፈጠራና ለኢኮኖሚ ብዝሃነት ያሉ የፋይናንስ አማራጮች" በሚል መሪ ሀሳብ ከግንቦት 3 እስከ 7 ቀን 2010 ዓ.ም በአፍሪካ የኢኮኖሚክ ኮሚሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ የሚካሄድ ይሆናል።

ጉባኤው ዘንድሮ ሲካሄድ ለ51ኛ ጊዜ ሲሆን የትኩረት አቅጣጫው የአፍሪካ ነጻ የጋራ ንግድ ቀጠናና ተጓዳኝ ጉዳዮች ይሆናሉ።

መጋቢት 12 ቀን 2010 በሩዋንዳ ኪጋሊ በተካሄደው 10ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች አስቸኳይ ስብሰባ የአፍሪካ ህብረት አባል አገሮች የአፍሪካ ነጻ የጋራ ንግድ ቀጠና ስምምነት መፈረማቸው ይታወሳል።

የሚኒስትሮቹ ስብስባ ግንቦት ስድስትና ሰባት ቀን 2010 የሚካሄድ ሲሆን በመሪ ሀሳቡ ላይ ተመስርቶበከፍተኛ ደረጃ የፖሊሲ ውይይት እንደሚደረግና በአፍሪካ አህጉር በኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ላይ እንደሚመክሩ ተገልጿል።

የአፍሪካን አገሮች የንግድና የኢኮኖሚ ትስስር ይበልጥ በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው በሚያሳድጉበት ሁኔታም ይወያያሉ ተብሏል።

የሚኒስትሮቹ ጉባኤ ከመካሄዱ በፊት ከግንቦት 3 እስከ 5 2010 የአፍሪካ አገሮች የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ስብሰባ እንደሚካሄድና ባለሙያዎቹ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎችን በማቅረብ ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

በተጨማሪም ግንቦት 5 ቀን 2010 ከጉባኤው ጎን ለጎን በአፍሪካ ኢኮኖሚ ዙሪያ ያተኮሩ ዝግጅቶች እንደሚኖሩ ተጠቁሟል።

በጉባኤው ማጠናቀቂያ 52ኛውን ጉባኤ የሚያስተናግድ አገር ይመረጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን በድረ ገጹ አስፍሯል።

በየዓመቱ የሚካሄደው ይህ የፋይናንስ፣ ዕቅድና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሮች ጉባኤ ባለፈው ዓመት በሴኔጋል ርዕሰ መዲና ዳካር ሲካሄድ፤ በአፍሪካ ኢኮኖሚ እድገትና በስራ አጥነት ቅነሳ ላይ ትኩረት አድርጎ መወያየቱ ይታወሳል።

ምንጭ፦ ኢዜአ