የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የዓለም ዓቀፉ አመታዊ የኢንቨስትመንት ጉባኤ ተሸላሚ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2010(ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ቀዳሚ የምስራቅ አፍሪካ ክፍለ አህጉር ውጤታማ የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ተቋም በመባል የዓለም ዓቀፍ ዓመታዊ የኢንቨስትመንት ጉባኤ አሸናፊ ሆነ።

የዓለም ዓቀፍ ዓመታዊ የኢንቨስትመንት ጉባኤ በየዓመቱ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ውጤታማ አፈፃፀም ያሳዩ ሃገራትን በማወዳደር የሚሸልም ተቋም ነው። 

 

ይህ ሽልማት በተመረጡ ዘርፎች ላይ የውጭ ባለሃብቶችን በመመልመል የቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰትን በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው ከፍተኛ የሆኑ ኢንቨስትመንቶችን በማስፋፋት አመርቂ ውጤት ላስመዘገቡ ሃገራትና የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ተቋማት የሚበረከት እንደሆነ ተጠቁሟል።

በዚህም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከሩዋንዳ አቻው ጋር በመወዳደር የምስራቅ አፍሪካ ክፍለ አህጉር ውጤታማ የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ተቋም በመባል ለ2018 የተዘጋጀውን አለም አቀፍ ሽልማት እንዳሸነፈ ነው ኮሚሽኑ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ ያስታወቀው።

ሽልማቱን በተባበሩት የአረብ ኤሚሬቶች የኢትዮጵያ ቆንስላ ጀነራል ወ/ሮ እየሩሳሌም ዓምደማርያም ኮሚሽኑን በመወከል በቦታው በመገኘት ሽልማቱን ተቀብለዋል።

ሽልማቱን በተቀበሉበት ወቅትም እንደተናገሩት፥ መንግስት የውጭ ኢንቨስትመንቶች የአካባቢ ጥበቃን ባማከለ፣ የወጪ ንግድን በሚያበረታታ፣ ከሃገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስርን እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በሚያፋጥን መልኩ በማሳለጥ ባሳየው ከፍተኛ አፈፃፀም ለሽልማት እንደበቃ ተናግረዋል።

እነዚህ ኢንቨስትመንቶችም አገሪቱ ያስቀመጠቻቸውን የኢኮኖሚ ዕድገት ዕቅዶችና ዓለም ዓቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ ቁልፍ መሳሪያዎች ሆነው እያገለገሉ እንደሆነም ገልፀዋል።

በዚህ ጉባዔ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የቤልጂየም፣ ህንድ፣ ሰርቢያ፣ ግብፅ፣ ጋና እና የስዋዚላንድ ኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ተቋማት በየክፍለ አህጉራቸው ቀዳሚ በመሆን እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

ሽልማቱ ተቋማቱ ሃገራቸውን በማስተዋወቅና መልካም ስም በመፍጠር ኢንቨስትመንትን ወደ ሃገራቸው በመሳብ የአገራቸውን ኢኮኖሚ በማሳደግና ስራ ፈጠራን በማስፋፋት ረገድ ላደረጉት ውጤታማ እንቅስቃሴ ማሳያ እንደሆነ የጉባኤው ፕሬዚዳንት ዻውድ አል ሼዛዊ ተናግረዋል።