ብሄራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካን ጨምሮ አራት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ወደ ግል ይዞታ ሊዛወሩ መሆኑ ተነገረ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 5፣ 2010(ኤፍ.ቢ.ሲ) በመንግሥት ይዞታ ሥር የነበሩ አራት ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ ሊያዘዋውር መሆኑን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ይህን የገለፀው የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸሙን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርብ ነው።

ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ በሁለተኛው የእድገትና ትራንፎርሜሽን እቅድ በተቀመጠው ስትራቴጂ መሰረት ወደ ግል ይዞታነት እንዲዞሩ ውሳኔ የተሰጠባቸው የልማት ድርጅቶችን ለማሸጋገር እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

ይህን ሽግግር በቀሩት የእቅድ ዘመኑ ሁለት ዓመታት ለማጠናቀቅ መታቀዱን ገልጸው በ2010 በጀት ዓመት ቀሪ የልማት ድርጅቶችን ለማዛወር እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራትም በእቅድ የተያዙ የልማት ድርጅቶች በቀጥታ ሽያጭና በጋራ ልማት ወደ ግል ይዞታ ለማዛወር የዝግጅት ሥራዎች ተከናውነዋል።

የብሄራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ፣ የቀንጥቻ ታንታለም ፋብሪካ፣ የፍል ውኃና ላንጋኖ ሪዞርት ሆቴሎች እንዲሁም በግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ሥር የሚተዳደረው የሻሎ እርሻ የዋጋ ትመና መጠናቀቁ ተነግሯል።

የሆቴሎች ልማት አክሲዮን ማህበርም የዋጋ ትመናም እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሸበሌ ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር፣ የአሰላ ብቅል ፋብሪካና የኢትዮጵያ ቆርኪና ጣሳ አክሲዮንን ወደ ግል ይዞታ ለማዛወር ጨረታ መውጣቱንና የአሰላ ብቅል ፋብሪካ አሸናፊው ተለይቶ 35 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ ተፈጽሞ ውል መፈረሙን አብራርተዋል።

ከኢትዮጵያ ቆርኪና ጣሳ አክሲዮንና ሸበሌ ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበራት ጋር በተያያዘም ሂደቱ ተጠናቆ ውሳኔ እንዲሰጥበት ለመንግሥት መቅረቡን ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ በበጀት ዓመቱ ወደ ግል ይዞታ ከተዛወሩ ውዝፍ ሽያጭና ቀሪ ክፍያ 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 13 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ገልጸዋል።

ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ በማዛወር ሥራ የተገኙ ልምዶችና የወደፊት ተግባራትን በተሻለ መንገድ ለማከናወን ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የፕራይቬታይዜሽን ፋይዳ ጥናት እየተካሄደ ነውም ብለዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክቶች፣ የማዳበሪያ ፋብሪካዎችና የሌሎች ሜጋ ፕሮክቶች አፈጻጸም መጓተት ለምን በፍጥነት አይፈታም ሲሉ ማብራሪያ ጠይቀዋል።

ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ ሜጋ ፕሮጀክቶች ከመጀመራቸው በፊት የአዋጪነት ዝርዝር ጥናት ስለማይካሄድ ለአፈጻጸም መዘግየት ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።

ይህም ከመሰረተ ልማት አቅርቦት ጀምሮ የካሳና የተጠቃሚነት ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ እንዳይመለሱ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ በሚጀመሩ አዳዲስ ፕሮጀክቶች መሰል ችግር እንዳይገጥም ተገቢው ጥናት እንደሚካሄድ አረጋግጠዋል።

የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) 10 የስኳር ፕሮጀክቶችን ግንባታ ለማከናወን ውል ፈርሞ ወደ ሥራ ቢገባም በተለያዩ ምክንያቶች በሚፈለገው ልክ ማከናወን እንዳልቻለም ሚኒስትሩ አመልክተዋል።

የስምንት ፕሮጀክቶች ውል ተቋርጦ በሌላ ተቋረጮች እንዲሰራ መደረጉን ጠቁመዋል።

የስኳር ፕሮጀክቶቹን ወደ ሥራ ለማስገባት በተደረገው ጥረት ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ከሞላ ጎደል ወደ ሥራ መግባታቸውንም አክለዋል።

ከያዮ ማዳበሪያ ፋብሪካ ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ ግምገማ መደረጉን የተናገሩት ዶክተር ግርማ በዚሁ መሰረት የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ የውሳኔ ሀሳብ ለመንግሥት መቅረቡን አስታውቀዋል።

ምንጭ፡- ኢዜአ