መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦችን በህገወጥ መንገድ ሲያሰራጩ በተገኙ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦችን ከአሰራር ስርዓቱ ውጪ በህገ ወጥ መንገድ ሲያሰራጩ በተገኙ የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን ንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ።

እርምጃ የተወሰደባቸው ስኳር፣ የምግብ ዘይትና የስንዴ ዱቄት ለተጠቃሚው ማህበረሰብ እንዲያሰራጩ በተመረጡ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት፣ ቸርቻሪ የግል ድርጅቶች፣ ሱፐርማርኬቶች እና ፋብሪካዎች ናቸው።

በንግድ ሚኒስቴር የገበያና የድርጅት ኢንስፔክሽንና ሪጉላቶሪ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ሙላት፥ በተመረጡ 163 የንግድ ተቋማት ላይ የተቀመጠውን የአሰራር ስርዓት ተከትለው ማሰራጨታቸውን ለማረጋገጥ የቁጥጥር ስራ ተሰርቷል ይላሉ።

በዚህም በአዲስ አበባ ከተማ በተደረገው ቁጥጥር ከተቀመጠው የአሰራር ስርዓት ውጪ ሲሰሩ የተገኙ 21 የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት እና 20 ቸርቻሪ የግል ሱቆች እርምጃ እንዲወሰድባቸው ጉዳያቸው ለከተማ አስተዳደሩ ተላልፏል ብለዋል።

በተመሳሳይ መልኩ ስኳር በአግባቡ ለህብረተሰቡ ስለማሰራጨታቻው ቁጥጥር ከተደረገባቸው 48 ሱፐር ማርኬቶች ውስጥ 47 ከመመሪያ ውጪ ሲሰሩ በመገኘታቸው ስኳር እንዳያከፋፍሉ ታግደዋል።

ዘይትን እንደ ግብዓት የሚጠቀሙ ስምንት ፋብሪካዎች ላይ ቁጥጥር ተደርጎ የእርምት እርምጃ ውሳኔ ለመስጠት በሂደት ላይ መሆኑንም አቶ ካሳሁን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ስኳርን በግብዓትነት የሚጠቀሙ 59 ፋብሪካዎች ላይ የቁጥጥር ስራ የተሰራ ሲሆን፥ 2 ፋብሪካዎች ስኳር እንዳያገኙ ታግደዋል።

5 ፋብሪካዎች ተጨማሪ ምርመራ እንዲካሄድባቸው፣ 52 ፋብሪካዎች ደግሞ 14 ሺህ 205 ኩንታል ስኳር ከኮታቸው እንዲቀነስባቸው ተደርጓል ብለዋል ዳይሬክተሩ።