የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ በሚቀጥለው ሰኔ ስራ እንደሚጀምር ተገለጸ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 04፣ 2010፣(ኤፍ.ቢ.ሲ)የመድሃኒት እና የህክምና መሳሪያ አምራች ኩባንያዎች የሚስተናገዱበት የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ በመጪዉ ሰኔ ወር ስራ እንደሚጀምር የኢንደስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ገለጸ።

የፓርኩ ግንባታ በተለያዩ ምክንያቶች ቢዘገይም በአሁኑ ሰዓት 70 በመቶ የተጠናቀቀ መሆኑን የኢንደስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን አስታውቋል።

ኢንደስትሪ ፓርኩ በ279 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፥ በ5 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ እየተገነባ እንደሆነ ነው የተገለጸው።

10 አለም አቀፍ የመድሃኒት አምራች ኩባንያዎች ወደ ፓርኩ ለመግባት ፍላጎታቸውን እንዳሳዩ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል።

ፓርኩ አለም አቀፍ ኩባንያዎችንም ለመሳብ የሚያስችል ደረጃውን የጠበቀ መሆኑም በኤጀንሲዉ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ አድናን በሬ ተናግረዋል።

የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች ከባንክ የብድር ትስስር እንዲኖራቸውና የማበረታቻ ድጋፍ በማድረግ በዘርፉ ላይ እንዲሰሩ ቢደረግም በቂ ውጤት እንዳልተገኘ ውይዘሮ አድና አስረድተዋል።

ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነዉ የመድሃኒት ፍጆታ ከዉጪ ተገዝቶ የሚገባ ሲሆን፥ ፓርኩ አገልግሎት ሲጀምር ከውጭ የሚገቡ መድሀኒቶችንና የህክምና መሳሪያዎች በሃገር ውስጥ በማምረት ለዜጎች የስራ እድልን በመፍጠር የውጭ ምንዛሬ ወጪን በመቀነስ ከፍተኛ አስተዋኦ እንደሚኖረው በኢንደስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተወዳዳሪነትና ስራ ፈጠራ ፕሮጀከት ዋና አስተባባሪ አቶ ተሰማ ገዳ ገልጸዋል።

ለዚህም መንግስት መድሃኒቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችለውን የቂሊንጦ የመድሃኒትና የህክምና መሳሪያ ማምረቻ ፓርክ ግምባታን ጀምሯል።

ግንባታው በአየር ጸባይ፣ በግብአት አቅርቦትና ሌሎች ምክንያቶች ቢዘገይም በአሁኑ ሰዓት 70 በመቶ ደርሷል፤ በሚቀጥለው ሰኔ ወርም ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተገልጿል።

ግንባታው የጉምሩክ፣ የጤና፣ የእሳት አደጋ መከላከልና ሌሎች አገልግሎቶችን በአንድ መስኮት ያቀፈና ከ15 እስከ 30 ሜትር ስፋት ያላቸዉ 17 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገዶችንም ያከተተ እንደሆነ ታውቋል።

ለዉጪ ባለሃበቶች የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ መሆኑን የሚናገሩት በኢትዮዽዩያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የፖሊሲ ጥናት ዘርፍ እና የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባየዉ፤ ፓርኩ በአለም አቀፍ ደረጃ ትላልቅ ስም ያላቸዉን ኩባንያዎች ቀልብ እየሳበ ሲሆን ከሚቀጥለው ሰኔ ወር ጀምሮ ተቀብሎ ያስተናግዳል ብለዋል።

በዚህ ሰዓትም 10 አለም አቀፍ የመድሃኒት አምራች ኩባንያዎች ወደ ኢንደስትሪው ገብተዉ ለመስራት ጥያቄ አቅርበዉ የግምገማ ስራ እየተሰራ መሆኑ ተመላክቷል።

የምርት ግብአቶችን ከቀረጥ ነጻ ከማስገባት ጀምሮ የግብር እፎይታ የገበያ ትሰስር መረጃና መሰል ማበረታቻዎችም በኢንደስትሪ ፓርኩ ገብተው ለሚያመርቱ ኩባንያዎች የሚሰጡ ይሆናል ተብሏል።

 

 

 

በሀይለሚካኤል አበበ