በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የፒዛ ሃት ሬስቶራንት በይፋ ተመርቆ ስራ ጀመረ

አዲስአበባ፣ ሚያዚያ 2፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ የሬስቶራንት ሰንሰለት የሆነው ፒዛ ሃት በኢትዮጵያ ትልቅ የምግብ ፍራንቻይዝ በመክፈት የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ድርጅት ሆኗል።

በምርቃቱ ስነ ስርዓቱ ላይ በኢትዮጵያ የአሜሪካን አምባሳደር ማይክል ሬይነር፣ የ“የም ብራንድስ ኢንክ.” ተወካዮች፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እንዲሁም ጥሪ የተደረገላችው እንግዶች ተገኝተዋል።

በኢትዮጵያ ፍራንቻይዝ ባለቤት የሆነው በላይ አብ ፉድስ እና ፕሮዳክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ነው ተብሏል።

አገልግሎቱንም በሁለት ቦታዎች ማለትም በሲኤምሲ እና ከፍተኛ እንቅስቃሴ በሚደረግበት በቦሌ መድሃኒዓለም አካባቢ በመክፈት ስራውን ጀምሯል።

የበላይ አብ ፉድስ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሚካኤል ገብሩ በኢትዮጵያ ውስጥ የተወሰኑ አህጉራዊ ፋራንቻይዝ ሬስቶራንቶች ቢገኙም፥ ፒዛ ሃት ግን ወደ ኢትዮጵያ ገበያ የገባ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የሬስቶራንት ፋራንቻይዝ ነው ብለዋል።

እንዲሁም በአሜሪካ ሀገር የሚገኙ የሬስቶራንቱ ቅርንጫፎች ከ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ግለሰቦች የስራ እድል የፈጠሩ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ 85 በመቶው ከ25 ዓመት በታች መሆናቸውን አብራርተዋል።

በላይ አብ ፉድስ ይህንን ባህል በመከተል ወጣቶች ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በመቅጠርና የተለያዩ ሀገራት ወስዶ ስልጠና በመስጠት ከፒዛ ሃት ብራንድ ጋር እንዲዋሀዱ ማድረጉን ገልጿል።

የምግብ ዝርዝሩ ፒዛ ሃት የሚታወቅባቸውን የፒዛ እና የሌሎች የምግብ ዓይነቶችን ያካተተ ነው።

እነዚህ ምግቦች የኩባንያውን ልዩ ጣዕምና ዓለም አቀፋዊ ጥራት ለመጠበቅ ሲባል ሙለ በሙለ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ በመጡ የምግብ ግብዓቶች የሚዘጋጁ ናቸው ተብሏል።

እንዲሁም ሬስቶራንቶቹ ዘመናዊነትን የተላበሱና የኩባንያውን ደረጃ ለመጠበቅ ሲባል ከውጭ በመጡ የመገልገያ እቃዎች አገልግሎት እንደሚሰጥ አቶ ሚካኤል ገልጸዋል።

እንደ አውሮፓውያን ዘመን በ1958 ዓ.ም በዊቺታ ካንሳስ የተመሰረተው ፒዛ ሃት በአሁኑ ወቅት ከመቶ በላይ ሀገራት ውስጥ ከ16 ሺህ 700 በላይ ሬስቶራንቶች ያለው ሲሆን፥ በቀላሉ ማዘዝ የሚቻልባቸው አማራጮች አሉት።