አየር መንገዱ ዘመናዊ የደህንነት መፈተሻ መሳሪያ አስመረቀ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 1 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የመጀመሪያ ነው የተባለውን ዘመናዊ የደህንነት መፈተሻ መሳሪያ በዛሬው እለት አስመረቀ።

የደህንነት ፍተሻ መሳሪያዎቹ ሁለት ሲሆኑ፥ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ዋጋ አላቸው ተብሏል።

መሳሪያዎቹ አየር መንገዱ ባለፉት አመታት ወደ አሜሪካ ላደረገው በረራ ከአሜሪካ መንግስት የተሰጠ መሆኑም በስነ ስርዓቱ ወቅት ተገልጿል።

መሳሪያዎቹ የሰዎችንና እቃዎችን የተለያየ ገጽታ ማሳየት የሚያስችሉ ሲሆን፥ የአየር መንገዱን ተመራጭነት እንደሚያሰፉም ታምኖበታል።

et_1.jpg

የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደገብረማርያም፥ መሳሪያው የደህንነት ፍተሻ አገልግሎቱን ለማቀላጠፍ እንደሚረዳ ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም በተለያዩ አጋጣሚዎች በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር የሚወጡ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ሀብቶችን ለመታደግ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ራይነር በበኩላቸው፥ ድጋፉ አሜሪካንና የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ግንኙነት ይበልጥ ያጠናክራል ብለዋል።

ሃገራቸውም ለአየር መንገዱ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል።

 

በቤተልሄም ጥጋቡ