ለግል ድርጅት የተሸጠው የአሰላ ብቅል ፋብሪካ የርክክብ ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአሰላ ብቅል ፋብሪካን ለግል ድርጅት ለማስረከብ የሚያስችል ስምምነት ዛሬ ተፈርሟል።

የመንግስት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር የአሰላ ብቅል ፋብሪካን ከገዛው ከኦሮሚያ ግብርና ህብረት ስራ ፌዴሬሽን ጋር ነው ስምምነቱን የተፈራረመው።

ስምምነቱንም የመንግስት ልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ እና የፌዴሬሽኑ ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ትርፌሳ ነጋሳ ናቸው የተፈራረሙት።

የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ረዳት ሃላፊ አቶ አሰበ ከበደ ለፋና ብሮድካስቲግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ ይህን ስምምነት ተከትሎ ፋብሪካውን በአካል ከ10 ቀናት በኋላ ርክክብ ይደረጋል።

ፋብሪካው ለኦሮሚያ ግብርና ህብረት ስራ ፌዴሬሽን በ1 ቢሊየን 343 ሚሊየን 660 ሺህ ብር መሸጡ ይታወሳል።

ፌዴሬሽኑ 35 በመቶ ክፍያውን ያከናወነ ሲሆን፥ ቀሪውን እስከ አምስት ዓመት ማጠናቀቅ ይጠበቅበታል።

አሰላ ብቅል ፋብሪካ አትራፊ ከሚባሉ ድርጅቶች መካከል ይመደባል።

 

በታሪክ አዱኛ