ምርት ገበያው ከደቡብ ግሎባል ባንክ ጋር የአገልግሎት ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 13፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ)የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የደቡብ ግሎባል ባንክን የክፍያ ፈፃሚ አጋሩ ለማድረግ የአገልግሎት ስምምነት ተፈራረመ።

ምርት ገበያው ከባንኮች ጋር ስምምነት በመፈራረም መስራቱ ተገበያዮች ግብይት በፈፀሙ ማግስት የሸጡበትን ገንዘብ በቀጥታ ከገዢው የባንክ ሂሳብ ወደ ሂሳባቸው ለማዘዋወር ያስችላል።

የደቡብ ግሎባል ባንክ በምርት ገበያው 13ኛ ክፍያ ፈፃሚ ባንክ በመሆን አገልግሎት ይሰጣል።

ስምምነቱን የምርት ገበያው ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወንድማገኘሁ ነገራና የደቡብ ግሎባል ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አዲሱ ሀባ ፈርመዋል።

የተደረሰው ስምምነት የክፍያ ስርዓቱን ይበልጥ ለማቀላጠፍና ለማዘመን የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት አስተዋፅኦ እንዳለው ተገልጿል።

ቡና አብቃይና አምራቾች በሚገኙባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች በርካታ ቅርንጫፎች ያሉት ባንኩ ለምርት ገበያው አባላትና ተገበያዮች አማራጭ እንደሚሆንም ተገልጿል።

ከሐምሌ 2009 ዓመተ ምህረት አንስቶ ተግባራዊ በተደረገው አዲሱ የቡና ግብይት ስርዓት አባል ያልሆኑ ቀጥታ ተገበያዮች በምርት ገበያው እንዲገበያዩ በመፈቀዱ ከባንኩ አገልግሎት አርሶ አደሮች፣ የህብረት ስራ ማህበራትና የግል ድርጅቶችም ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል።

በሃዋሳና በተለያዩ ከተሞች በቅርቡ የሚከፈቱት የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ማዕከላት እንዲሁም በቡሌ ሆራና አካባቢዎች የሚከፈቱት የምርት መቀበያ ቅርንጫፎች ከፍተኛ የገንዘብ እንቅስቃሴ ስለሚፈልጉ ከባንኮች ጋር ያለውን ግንኙነት እንደሚቀጥልም ምርት ገበያው ገልጿል።

የደቡብ ግሎባል ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አዲሱ ሀባ በበኩላቸው ባንካቸው ከምርት ገበያው ጋር በጋራ መስራት መጀመሩ ተገበያዮች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል።

በተለይም ባንኩ የቡና አብቃይ አምራቾች በሚገኙባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች በርካታ ቅርንጫፎች ያሉት በመሆኑ አምራቾች በቀላሉ የመገበያያ አማራጮችን ያገኛሉ ነው ያሉት።

ስምምነቱ መካሄዱ ግብይቱ በመተማመን ላይ የተመሰረተ እንዲሆንና ዘመናዊ የክፍያ ስርአት እንዲኖረው ያደርጋል መባሉ ኢዜአ በዘገባው አንስቷል።