የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ከሶስት ወራት በኋላ ወደ ስራ ይገባል

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 10 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ከሶስት ወራት በኋላ ወደ ስራ ይገባል።

በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ በመገንባት ላይ ከሚገኙት ፓርኮች ውስጥ የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንደስትሪ ፓርክ አንዱ ነው።

ባለፈው አመት መጋቢት ወር ላይ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት ፓርክ፥ በ294 ነጥብ 5 ሄክታር ላይ ግንባታው እየተካሄደ ነው።

በክልሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተቀናጀ አግሮና ልዩ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኦፕሬሽን አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ናትናኤል ሚሊየን ፓርኩ 59 ሼዶች እንዳሉት ተናግረዋል።

ሙሉ ለሙሉ ተገንብቶ ሲጠናቀቅም ከ393 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ሰዎች የስራ እድል ይፈጥራል ነው ያሉት።

የፓርኩ የመጀመሪያ ምእራፍ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፥ አሁን ላይ የባለሃብቶች ምልመላ እየተካሄደ ነው ብለዋል።

አሁን ላይም በፓርኩ ሶስት የውጭ ኩባንያዎች የራሳቸውን ጥናት በማካሄድ የቅድመ ምርት ስራ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

ፓርኩ በ100 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ የገጠር ለውጥ ማዕከላት ግንባታዎች እየተከናወኑለት ሲሆን፥ ማዕከላቱ የግብርና ምርቶችን ከአርሶ አደሮቹ ተቀብለው ደረጃ የማውጣት፣ የመለየትና በከፊል የማጠናቀቅ ስራዎች የሚሰራባቸው ናቸው።

ግንባታው ሲጠናቀቅም በክልሉ በስፋት የሚመረተውን አትክልትና ፍራፍሬ በማቀነባበር የአካባቢውን አርሶ አደሮች በእጅጉ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

ወደ ስራ ሲገባም የቡና፣ አቮካዶ፣ የስጋ እና የወተት ምርቶችን ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ በማቀነባበር ለውጭ ገበያ ያቀርባል።

የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች የሚቋቋሙበት፣ ፋብሪካዎችን የሚመግቡ በ1 ሺህ ሄክታር መሬት ዙሪያ የሚገነቡ የገጠር ትራንስፎርሜሽን ማዕከላት እና የአርሶ አደሩን ምርቶች የሚሰበስቡ ማዕከላትን ያካተቱ ሶስት ዋና ዋና ክፍሎች ይኖሩታል።


በትዕግስት ስለሺ