ተቋሙ በንግድ ሥራ ለሚሰማሩ ሴቶች 150 ሚሊየን ብር ብድር ሰጠ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ ክልል በአነስተኛ የንግድ ሥራ ለሚሰማሩ ሴቶች 150 ሚሊየን ብር ብድር መስጠቱን የክልሉ አነስተኛ ፋይናንስ ተቋም አስታወቀ።

አንድ ሺህ 500 የክልሉ ሴቶች የብድር አገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆነዋል።

ገንዘቡን ለተጠቃሚዎች ለመስጠት ትናንት በጅግጅጋ ከተማ በተዘጋጀ ስነስርአት ላይ እንደተገለጸው፥ የብድሩ ተጠቃሚ በመሆን በንግድ ሥራ የሚሰማሩት ሴቶች በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ገንዘቡን ሰርተው መመለስ ይጠበቅባቸዋል።

የብድሩ ተጠቃሚዎች ተቋሙ በክልሉ ህጋዊ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲጠናከር ከማድረግ ባለፈ ሰርተው መለወጥ ለሚፈልጉ ሴቶች የመንቀሳቀሻ ገንዘብ በብድር በመስጠት እያደረገ ያለው ድጋፍ ሊበረታታ እንደሚገባም አመልክተዋል።

የሶማሌ ክልል አነስተኛ ፋይናንስ ተቋም ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ከድር መሐመድ፥ 150 ሚሊየን ብር በህጋዊ የንግድ ሥራዎች ለሚሰማሩ 1 ሺህ 500 ስራ አጥና አነስተኛ ገቢ ላላቸው ሴቶች በብድር መሰጠቱን ጠቁመዋል።

ተቋሙ የሥራ አጥ ሴቶችን ኢኮኖሚ አቅም ለማሳደግ የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያጠናክር ገልጸው፥ ሴቶቹ ከ93 ወረዳዎችና ከስድስት ከተማ መስተዳድሮች የብድር መስፈርቱን አሟልተው የተመረጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አቶ ከድር እንዳሉት ቀደም ሲል ብድር የወሰዱ የተቋሙ ደንበኞች 155 ሚሊየን ብር ቆጥበዋል።

ተቋሙ በክልሉ ድህነትን ለመቀነስና ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት በድህነት ወስጥ ላሉ አምራች የህብረተሰብ ክፍሎች ዘመናዊ የቁጠባና የብድር አገልግሎቶችን ለመስጠት አልሞ እየሰራ መሆኑን ኢዜአ በዘገባው አንስቷል።