መንግስት የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርአት ተግባራዊ ሊያደርግ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የመንግስት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርአት ተግባራዊ ሊያደርግ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የኤጀንሲው ህዝብ ግንኙነት ዳዬሬከተር አቶ ሰጠኝ ገላን፥ ስርአቱን መዘርጋት ያስፈለገው በሀገር ደረጃ የሚመደበው ከፍተኛ በጀት ግዥ ላይ የሚውል በመሆኑ የግዥ ስርአቱ ከሰው ንክኪ ውጭ በማድረግ ከሙስና እና ብልሹ አሰራሮች ነፃ ለማድረግ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱን ወደ ስራ ለማስገባት የሰው ሃይል ቅጥርና እና የፕሮጀክት ጽህፈት ቤት የማቋቋም ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

የፕሮጀክቱን አፈፃፀምን ለመከታተል ከ9 የፌደራል ተቋማት የተወጣጣ አስተባባሪ ኮሚቴ መዋቀሩም ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ከአስተባባሪ ተቋማት መካከል እንሚገኙበት ተጠቅሷል፡፡

አዲሱ የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርአት በቀጣዩ አመት ወደ ተግባር ይገባል የተባለ ሲሆን÷ ከጊዜ እና ከአሰራር ጋር ሲነሱ የነበሩ ችግሮችንም ይፈታል ነው የተባለው፡፡

 

በተመስገን እንዳለ