ከአማራ ክልል ወደ ውጭ ገበያ ከተላኩ ምርቶች ከ154 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማራ ክልል ወደ ውጭ ሃገራት ከተላኩ የግብርናና ኢንዱስትሪ ምርቶች ከ154 ነጥብ 7 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ገቢ መገኘቱን የክልሉ ንግድ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስታወቁት፥ ምርቶቹ የተላኩት በ2010 ዓ.ም የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት ነው።

ከተገኘው ገቢ ውስጥ 142 ነጥብ 9 ሚሊየን ዶላሩ ከሰሊጥ፣ ቦለቄ፣ ጥራጥሬና መሰል የግብርና ምርቶች የተገኘ ነው።

ለገበያ ከቀረበው 1 ሺህ ቶን አበባ ሽያጭ ደገሞ ከ4 ነጥብ 6 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል።

ቀሪው ጨርቃ ጨርቅን ጨምሮ ከሌሎች የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች ሽያጭ የተገኘ መሆኑን ሀላፊው ተናግረዋል ።

"ከኢንዱስትሪና ከእንስሳት የተገኘው ገቢ የሚጠበቀውን ያህል አይደለም " ያሉት ሀላፊው ወደፊት የላኪዎችን አቅም በማጎልበት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የተገኘው የውጭ ምንዛሬ ገቢም የእቅዱን 89 ነጥብ 1 በመቶ ያሳካ መሆኑን ጠቁመዋል ።

እስከ በጀት አመቱ መጨረሻ ከክልሉ ለውጭ ገበያ ከሚቀርቡ የግብርናና ኢንዱስትሪ ምርቶች ሽያጭ ከ347 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነ ታውቋል ።

ምንጭ፦ ኢዜአ