በሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራትና በግል የስጋ መሸጫ ቤቶች የህብረተሰቡን ጥቅም በሚጎዳ መልኩ የሚዛን ማታለል እየተፈፀመ ነው-ጥናት

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት እና በግል የስጋ መሸጫ ቤቶች የህብረተሰቡን ጥቅም በሚጎዳ መልኩ የሚዛን ማታለል እየተፈጸመ መሆኑን አንድ ጥናት አረጋገጠ።

ይህ የተገለጸው የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን በክብደት መለኪያዎች ላይ የማታለል ተግባርን በተመለከተ ያደረገውን ጥናት ዛሬ ይፋ ሲያደርግ ነው።

ጥናቱ 110 በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የሸማች ህብረት ስራ ማህበራትና የግል ስጋ ቤቶች እንዲሁም በችርቻሮ ሱቆች ላይ የተከናወነ ነው ተብሏል።

ጥናቱን ያቀረቡት በመስርያ ቤቱ የጥናት እና ምርምር ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ሞላ እንዳሉት፥ በክብደት ልኬት መሳርያዎች የሚያጋጥም ስህተት እንዳለ ሆኖ ነገር ግን አሁን ጥናት በተደረገባቸው የከፋ ችግር አለባቸው የተባሉት 83 በመቶ የሚሆኑ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ናቸው።

እንዲሁም በግል ስጋ ቤቶች 52 በመቶ የሚሆኑት ችግሩ እንዳለባቸው ጥናቱ አመላክቷል።

ይህም ከአንድ ኪሎ ስጋ እስከ 143 ግራም የሚደርስ ጉድለት ተገኝቷል።

ይህ ችግር እንዳይፈጠር ቁጥጥር የሚያደርጉ ንግድ ሚኒስቴርን የመሰሉ አካላት፣ በየደረጃው ያሉ የንግድ ቢሮዎች እና ፅህፈት ቤቶች የክብደት ሚዛንን በቋሚነት አለመቆጣጠራቸው እና ድንገተኛ ፍተሻዎች አለመኖራቸው ተጠቁሟል።

ቁጥጥሮች ቢኖሩም ደግሞ የታዩት ጉድለቶችን በቸልታ ማለፍ እንደሚታይ በድክመት ተነስቷል።

በተጨማሪም የተጠናከረ እና የተደራጀ መረጃ አለመኖር፣ ችግር የተገኘባቸውን ነጋዴዎች አስተማሪ እርምጃ እና ማስተካከያ እንዲሰጥ አለመደረጉ በክፍተትነት ተነስቷል።

ህጉን የማስተግበርያ አዋጅም በንግድ ሚኒስትር የተቀረፀ ሲሆን፥ ይህም ከተወካዮች ምክር ቤት ደርሶ መፅደቅን እየጠበቀ ይገኛል ነው የተባለው።

ጥናቱን መሰረት በማድረግም ባለስልጣኑ ከፌዴራል እና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በጋራ በመሆን የሸማች ማህበረሰቡን መብት ለማስጠበቅ እንደሚሰራ ተገልጿል።

በኤርሚያስ ፍቅሬ