በኦጋዴን የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ወደ ጅቡቲ የሚያስተላልፍ የቧንቧ ዝርጋታ ውል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦጋዴን የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ወደ ጅቡቲ የሚያስተላልፍ የቧንቧ ዝርጋታ ውል ስምምነት ተፈረመ።

ስምምነቱን የተፈራረሙት የማዕድን፣ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴርና የቻይናው ፖሊ ጂ ሲ ኤል ኩባንያ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የተፈጥሮ ጋዙ ጥቅም ላይ በሚውልባቸው ጉዳዮች ላይ ከኩባንያው ፕሬዚዳንት ባርቶን ዩ ጋር መወያየታቸውም ተገልጿል።

ፖሊ ጂ ሲ ኤል ኩባንያ በኦጋዴን ተፋሰስ ውስጥ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ለመፈለግ ከአውሮጳውያኑ ዘመን ቀመር 2013 ጀምሮ ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል።

የማዕድን ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ የተፈጥሮ ጋዙን ለመፈለግ አስራ አንድ ጉድጓዶች የተቆፈሩ ሲሆን፥ እስካሁን ባለው ሂደት ከ5 እስከ 6 ትሪሊየን ኪዩቢክ ጫማ የተፈጥሮ ጋዝ ማግኘት መቻሉ ገልፀዋል።

የኩባንያው ኃላፊዎች የተፈጥሮ ጋዙ ወደ ጅቡቲ አልፎም ወደ ቻይና በሚሄድበት ጉዳይ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ጋር ውይይት ማድረጋቸውን የተናገሩት አቶ ሞቱማ፥ እስከ ጅቡቲ ወደብ የሚዘልቅ የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ ለመዘርጋት ስምምነት መደረጉን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ አራት ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ዶላር የተመደበለት ሲሆን፥ የተፈጥሮ ጋዙን ለመፈለግ 360 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጓል።

ፕሮጀክቱ ወደ ስራ ሲገባ ኢትዮጵያ በዓመት አንድ ነጥብ አራት ቢሊየን ዶላር ታገኛለች ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፥ በቀጣይ ዓመታት የሚገኘው ገቢ እስከ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል ተብሎ እንደሚገመት አቶ ሞቱማ ገልጸዋል።

የቧንቧ ዝርጋታው በኦጋዴን አካባቢ በነዳጅ ፍለጋ ለተሰማሩ ሌሎች ኩባንያዎችም የሚያገለግል መሆኑንም ነው ሚኒስትሩ ያብራሩት።

ሚንስትሩ የቧንቧ ዝርጋታው በኢትዮጵያ መንግስት ብቻ የሚወሰን አለመሆኑን ጠቁመው፥ 84 ኪሎ ሜትር በጅቡቲ ድንበር የሚዘረጋ መሆኑን ተናግረዋል።

ከጅቡቲ መንግስት ጋር የተለያዩ ድርድሮችን በማድረግ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱንም ጠቁመዋል።

የኩባንያው ፕሬዚዳንት ባርቶን ዩ በበኩላቸው፥ የቧንቧ ዝርጋታውን በተያዘው የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ እንደሚሰሩ ነው ያስታወቁት።

ፕሮጀክቱ በተያዘው ዓመት አጋማሽ የሚጀመር ሲሆን፥ በ2020 ተጠናቆ ወደ ስራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የኬንያውን ሳምር ግሩፕ ሊቀመንበር ናውሼድ ሚራሊን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ሊቀ መንበሩ በአማራ ክልል የብርጭቆ ፋብሪካ ለማቋቋም ቦታ የተረከቡ ሲሆን፥ በቅርቡ ወደ ስራ ለመግባት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒሰትር ኃይለማርያም በበኩላቸው ኢትዮጵያ ያላትን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመጠቀም ለሚመጡ ባለሃብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ መግለጻቸውን ውይይቱን የተከታተሉት በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አብራርተዋል።

ምንጭ፦ ኢዜአ