በአማራ ክልል ለህዳሴው ግድብ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ለማሰባሰብ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የህዳሴው ግድብ ችቦ አማራ ክልል መግባቱን ተከትሎ ለአንድ ወር በሚያደርገው ቆይታ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማሰባሰብ ታቅዶ እየተሰራ ነው።

የክልሉ የህዳሴው ግድብ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ላቀ ጥላዬ እንደገለጹት፥ የህዳሴ ግድብ ችቦ ከቆየበት ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ወደ አማራ ክልል አዊ ዞን እንጅባራ ከተማ ጥር 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ሲገባ በህዝቡ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።

"ወደ ክልሉ ከገባበት ጊዜ ጀምሮም በአዊና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች በመዘዋወር ላይ ነው" ብለዋል።

በተለይም በቻግኒ ከተማ አስተዳደርና ዙሪያውን ባሉ ወረዳዎች ነዋሪዎች ለችቦው ያደረጉት ደማቅ አቀባበልና በቦንድ ግዝ ያሳዩት ተሳትፎ በአርያነቱ ተጠቃሽ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።

ይፋዊ አቀባበል በተደረገበት በእንጅባራ ከተማም የህዳሴው ግድብ የድል ችቦ አደባባይ መሰየሙን የገለፁት ኃላፊው የአደባባዩ ግንባታ የህዳሴውን ግድብ አጉልቶ በሚያሳይ መልኩ የሚካሄድ መሆኑን አመላክተዋል ።

ችቦው ትናንት በምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተሰላም ከተማ በገባበት ወቅት ከ550 ሺህ ብር በላይ የቦንድ ግዥ መፈፀሙን የገለፁት ደግሞ የዞኑ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አንማው ዳኛቸው ናቸው።

"በዞኑ ከበጋ ወራት የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ ጋር በማስተሳሰር በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ 20 ሚሊየን ብር ገቢ ለማሰባሰብ ታቅዶ እየተሰራ ነው" ብለዋል።

በፍኖተ ሰላም ከተማ በመድኃኒት ንግድ ስራ የሚተዳደሩት አቶ ቴዎድሮስ ጌታሁን እንደገለፁት ከዚህ በፊት ለህዳሴው ግድብ ድጋፍ የሚውል የ20 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን አስታውሰዋል።

"የችቦውን ወደ ከተማው መግባት በማስመልከትም ተጨማሪ የ3ሺህ ብር ቦንድ ገዝቻለሁ" ብለዋል።

አቶ መንግስቱ ባየህ የተባሉት ነዋሪ በበኩላቸው የችቦውን አቀባበል በመስመልከት ለሶስተኛ ጊዜ የአንድ ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደምም ለታላቁ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ድጋፍ በሁለት ዙር የወር ደሞዛቸውን በመስጠት የቦንድ ግዥ መፈፀማቸውንም ጠቅሰዋል።

ግድቡ ሁሉንም የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦችን በአንድነተ በማስተሳሰር ሀገሪቱን ወደ ተሻለ የዕድገት ደረጃ የሚያሸጋግር በመሆኑ በቀጣይ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል።

ችቦው በክልሉ 12 ዞኖችና ከተሞች እየተዘዋወረ ለአንድ ወር በሚያደርገው ቆይታ ከ60 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ለማሰባሰብ ታቅዷል፤ ቀጥሎም ችቦው ወደ ትግራይ ክልል እንደሚያመራ ታውቋል።

 

 

ምንጭ፦ኢዜአ