55 የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ስራ ለመጀመር በዝግጀት ላይ ናቸው

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 8፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 55 የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ኩባንያዎች በ4 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በኢትዮጵያ ውስጥ ስራ ለመጀመር በዝግጀት ላይ መሆናቸውን አምባሳደር ጋዚ አብዱላ ቢናሹር ተናገሩ።

በኢትዮጵያ የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬትስ አምባሳደር ጋዚ አብዱላ ቢናሹር እንደተናገሩት፥ የኢትዮጵያእና የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ግንኙነት መጠናከር የሀገሪቷ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ ያላቸውን ኢንቨሰትመንት እንዲጨምር አድርጓል።

እስካሁን ባለው ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት፣ ወደ ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ከመጡት 103 የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ኩባንያዎች ውስጥ 48 ወደ ሥራ መግባታቸውንም አምባሳደሩ አስታውቀዋል።

55 ኩባንያዎች ደግሞ በ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በኢትዮጵያ ውስጥ ስራ ለመጀመረም በዝግጀት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።

አምባሳደር ጋዚ አብዱላ ቢናሹር፥ የኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬት ሁለንተናዊ ግንኙነት እና የትብብር አጀንዳዎች እየጨመሩ መምጣቱንም ተናግረዋል።

በሁለቱ አገራት መካከል እየተፈጠረ ባለው የተጠናከረ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት በርካታ የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬት ባለኃብቶች ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ነው ብለዋል።

በሥራ ላይ የሚገኙ ኩባንያዎች በምርት ማቀነባበሪያ ዘርፍ፣ በዘመናዊ ግብርና፣ በመድኃኒት ማምረቻ፣ በማዕድን ዘርፍ እና ሌሎች መስኮች ላይ መሰማራታቸውን አምባሳደሩ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ካላት ምቹ የኢንቨስትመንት ተመራጭነት በቀጣይም በርካታ ባለኃብቶች መዋለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እያሳዩ መሆናቸውን አምባሳደር ቢናሹር ገልፀዋል።

ሁለቱ አገራት በንግድና ኢንቨስትመንት ያላቸውን ግንኙነት ከማጠናከር አኳያ በጥምር ኮሚቴ ብዙ ሥራዎችን እያከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል።

የጋራ ትብብሩን ለማጠናከር የሁለቱ አገራት መሪዎች በቅርበት ውይይት እያደረጉ መሆኑን አንስተው፤ አገራቱ ያላቸው የጋራ ግንኙነት ከዚህ በላይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነት እንዳላቸውም አምባሳደር ጋዚ አብዱላ አስረድተዋል።

የሁለቱ አገራት ግንኙነት ከተጀመረ የቆየ ቢሆንም ኢትዮጵያ ቆንስላዋን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2004 በዱባይ የከፈተች ሲሆን፥ ኤምባሲዋን ደግሞ በ2014 በአቡ ዳቢ ከፍታለች።

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬት ደግሞ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2010 ነበር ኤምባሲዋን በኢትዮጵያ የከፈተችው።

የኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ የንግድ ግንኙነት ከ10 ዓመት በፊት ከነበረበት 45 ነጥብ 4 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ዶላር ባሳለፍነው የፈረንጆች 2016 ዓመት ከ809 ሚሊየን ዶላር በላይ መድረሱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ ያስረዳል።

ምንጭ፦ ኢዜአ