የኦሮሚያ ክልል በ8 ባለሃብቶች ያለአገልግሎት የተያዘ 180 ሄክታር መሬት አስመለሰ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 26፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል ለረዥም ጊዜ በስምንት ባለሃብቶች ያለአገልግሎት ታጥሮ የተያዘ 180 ሄክታር መሬት ማስመለሱን የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።

በጂማ ሰኮሩ ወረዳ ጨምሮ በምስራቅ ሸዋ፣ ሰሜን ሸዋ እና በምራብ ሸዋ ዞኖች ነው መሬቱ የተነጠቀው።

የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር አቶ ረሽድ ሙሃባ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ ባለሃብቶቹ ወደ ልማት እንዲገቡ፣ ለስራ አጦችም የስራ እድል እንዲፈጥሩ እና ራሳቸውም ተጠቃሚ

እንዲሆኑ በተደጋጋሚ ድጋፍ ቢደረግላቸውም መተግበር አልቻሉም።

በዚህም በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጣቸው ከተደረገ በኋላ የያዙት መሬት እንዲነጠቅ መደረጉ ተነግሯል።

በዚህ መልኩ ያለአገልግሎት ታጥረው ተይዘው ከነበሩት መካከል 32 ሄክታር በኢንዱስትሪ ዘርፍ፣ 83 ሄክታር በግብርና እና 10 ሄክታር ደግሞ ለአገልግሎት የተያዙ ይዞታዎች ይገኙበታል።

 

በታሪክ አዱኛ