የማር ምርታማነትን ለማሳደግ አመራረቱን ማዘመን እንደሚገባ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 22፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የማር ምርትን ከፍ ለማድረግ ከባህላዊ አመራረት ዘዴ ወደ ዘመናዊ እንዲሸጋገር በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የእንስሳት እና አሳ ሀብት ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሀገሪቱ ከፍተኛ ማር የማምረት አቅም ቢኖራትም ዘርፉን በቴክኖሎጂ ለማገዝ የተደረገው ጥረት ውስን በመሆኑ በሀገሪቱ በ2009 ካመረተችው 87 ነጥብ 6 ሺህ ቶን ማር 93 በመቶው በባህላዊ ዘዴ የተገኘ ነው።

ከ10 ዓመት በፊት የዘርፉን ምርት ከፍ ለማድረግ የሰለጠነ ባለሞያ ከማፍራት ጎን ለጎን በመጠቀም ባህላዊ ዘመናዊ የፍሬም ቀፎ ለመጠቀም ቢሰራም፤ የሚፈለገው ውጤት ማምጣት እንዳልተቻለ ተነግሯል።

በየእንስሳት እና አሳ ሀብት ሚኒስቴር የማርና ሀር ልማት ተወካይ ዳሬክተር አቶ ደምሰው ዋቅጅራ፥ የቴክኖሎጂ ሽግግሩ ውጤታማ እንዲሆን የኤክስቴንሽን አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ ወሳኝ ነው ይላሉ።

ከንብ አናቢው ጀምሮ በተዋረድ ያሉ ባለሞያዎች በዘርፉ ብቁ እንዲሆኑ በሀገሪቱ በዩኒቨርሲቲም ሆነ ቴክኒክ እና ሞያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጆች እየተሰጠ ያለ ቢሆንም በተግባር የተደገፈ አይደለም ብለዋል።

አቶ ደምሰው ዋቅጅራ፥ የቀፎ አመራረት ጥራት ማነስ በተጨማሪ የዋጋው ውድ መሆን ንብ አናቢው በተፈለገው ደረጃ እንዳይጠቀም አድርጎታል ሲሉም ተናግረዋል።

ዘርፉን ችግር ለመፍታት የማኒፋክቸሪንግ፣ የእስሳት እና አሳ ሀብት ሚኒስቴር እና የህብረት ሰራ ማህበራት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ነው የተባለው።

በሩብ ዓመቱ ወደ ውጭ ለመላክ ካቀደው 216 ቶን የማር ምርት 125 ነጥብ 3 ቶን ከእቅዱ 58 በመቶ ብቻ ነው የተሳካው።

በመላ ሀገሪቱ 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ማር አምራቾች ያሉ ሲሆን፥ በዚህ በጀት ዓመት 98 ነጥብ 6 ሺህ ቶን ማር ለማምረት እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው።

በሰርካለም ጌታቸው