የውጭ ባለሃብቶችን የውጭ ምንዛሬና የቪዛ ችግሮች እንደሚፈታ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 21፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የውጭ ሀገራት ባለሃብቶችን በውጭ ምንዛሬ እጥረት እና በቪዛ ጉዳዮች የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ከውጭ ባለሃብቶች ማህበራት ጋር በውጭ ምንዛሬ እጥረት እና በቪዛ ጉዳዮች ላይ በአዲስ አበባ ተወያይቷል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፍፁም አረጋ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፥ ኢትዮጵያ ለባለሃብቶች እና ለመሰረተ ልማት ግንባታ በሰጠችው ትኩረት ባለፉት ጥቂት አመታት በኢንቨስትመንት ዘርፍ ከፍተኛ ውጤት አግኝታለች።

የመንግስታቱ ድርጅት የ2016 ሪፖርት አፍሪካ 59 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ኢንቨስትመንት የሳበች ሲሆን፥ 3 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላሩ የኢትዮጵያ ድርሻ እንደነበር ኮሚሽነሩ ገልፀዋል።

አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከአለም ባንክ እና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተገኙት ሽልማቶችም ኢትዮጵያ በዘርፉ ትኩረት ሰጥታ ለመስራቷ ዋነኛ ምስክሮች መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢኮኖሚውን እድገት ዘላቂ ማድረግ፣ ለኢንቨስትመንት ትኩረት መስጠትና ማስፋፋት አስፈላጊ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ፍጹም፥ የባለሃብቶችን ችግር የመፍታት ጉዳይ የመንግስት አጀንዳ ነው ብለዋል።

ኮሚሽነሩ ከባለሃብቶች ማህበራት ጋር በመገናኘት ችግሮችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት እንደሚፈቱ ነው የተናገሩት።

በውይይቱ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና ከቪዛ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ለባለሃብቶች  ችግር መሆናቸው ተነስቷል።

አቶ ፍፁም አረጋ የወጪ ምርትን ለማሳደግ የብርን የመግዛት አቅም ማዳከም፣ ለውጭ ባለሃብቶች ያለ መገበያያ ሰነድ ከባንክ ውጭ በሚያገኙት ገንዘብ ''ፍራንኮ ቫሉታ'' በተባለው ስርዓት የግንባታ እቃዎችን እና ማሽነሪዎችን የመሳሰሉ የካፒታል እቃዎችን እንዲገዙ መፈቀዱ የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን ይቀንሰዋል ብለዋል።

የውጭ ምንዛሬ እደላ ከብሔራዊ ባንክ በተጨማሪ የግል ባንኮችም እንዲሳተፉ መደረጉ፣ ላኪዎች ከውጭ ካመጡት የውጭ ምንዛሬ የሚያስቀምጡት ከ10 በመቶ ወደ 30 በመቶ ከፍ መደረጉ እጥረቱን ለመቀነስ የተወሰደ ሌላው እርምጃ እንደሆነ ገልፀዋል።

ባለሃብቶች የኢንቨስተር ቪዛ ስለማያገኙ በቱሪስት ቪዛ እየመጡ ህጋዊ የሆኑ ስራዎችን ለመስራት ተቸግረው እንደነበር እና በትክክለኛ ቪዛ እንዲመጡ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከቪዛ ጋር ያለውን ችግር ለመቅረፍ በኢትዮጵያ ኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች መምሪያ በኩል ለቱሪስቶችና ለኮንፈረንስ ተሳታፊዎች መሰጠት የተጀመረው የኦን ላይን የኢ-ቪዛ አገልግሎት በቅርቡ ለባለሃብቶች እንደሚጀመር ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ ባለሃብቶች የሚገጥሟችውን ችግሮች ለመፍታት በየስድስት ወሩ ከውጭ ባለሃብቶች ማህበራትጋር እንደሚወያይ የተገለፀ ሲሆን በስብሰባው በኮሚሽኑ እውቅና ያገኙት የአሜሪካ፣ የአውሮፓ፣ የኔዘርላንድ የፈረንሳይ ኢንቨስተሮች ማህበር እንዲሁም በመቋቋም ላይ ያሉት የህንድና የቻይና ኢንቨስተሮች ማህበር ተሳትፈዋል።

 

ምንጭ፦ ኢዜአ