የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለደንበኞቹ ከ159 ቢሊየን ብር በላይ ማበደሩን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 19፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለደንበኞቹ ከ159 ቢሊዮን ብር በላይ ማበደሩን አስታወቀ።

የባንኩ የተመሰረተበትን 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓል አስመልክቶ ዛሬ በአዲስ አበባ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

ይኸው በዓል በአገር አቀፍ ደረጃ ከመጪው ቅዳሜ ጀምሮ ለቀጣዮቹ ስድስት ወራት በተለያዩ መርኃ ግብሮች እንደሚከበር በመግለጫው ላይ ተገልጿል።

የባንኩ የሰው ኃይል አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሰይፉ ቦጋለ እንደተናገሩት በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት የባንኩ የገንዘብ አቅም እያደገ መጥቷል።

በአውሮፓውያኑ 2011 የባንኩ የማበደር አቅም ከ16 ቢሊዮን ብር በታች የነበረ ሲሆን፥ በ2017 ግን ባንኩ ለልማት ፕሮጀክቶች፣ለግለሰብ ድርጅቶችና መሰል ስራዎች ያበደረው የገንዘብ መጠን ከ159 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል።

በአሁኑ ወቅት የባንኩ ተቀማጭ የገንዘብ መጠንም ወደ 400 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተገልጿል።

ባንኩ በመላው አገሪቱ ተደራሽነቱን ለማስፋፋትም በየአመቱ በአማካይ 150 ቅርንጫፎች ለመክፈት የአምስት አመት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ መሰረት እየሰራ መሆኑን አቶ ሰይፉ ተናግረዋል።

በዚህም የባንኩን የቅርንጫፍ ብዛት ከሰባት አመት በፊት ከነበረበት 220 ወደ 1 ሺህ 240 በላይ ማድረስ ሲቻል የደንበኞቹን ቁጥርም ከ16 ሚሊዮን በላይ ሲያደርስ የኤቲ ኤምና ፖስት ማሽን ተጠቃሚዎች ቁጥርም ከ4 ሚሊዮን በላይ ደርሷል።

በአሁኑ ወቅት ባንኩ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ፣ ለጊቤ ሶስት ፣ ለገናሌ ዳዋ ፣ ለአዳማ የንፋስ ኃይል፣ለጣና በለስ እና ሌሎች ፕሮጀክቶችን በመደገፍ ረገድም ባንኩ እያደረገ የሚገኘውን አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ምክትል ፕሬዘዳንቱ ገልጸዋል።

የነዳጅና የማዳበሪያ ግዢዎችን በማመቻቸት፣የዜጎችን የቤት ባለቤትነት በማገዝ፣ለሆቴሎች ግንባታና ሌሎች ኢንቨስትመንቶችን ብድር በማቅረብ ለአገሪቱ የሕዳሴ ጉዞ የሚጠበቅበትን እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

በባንኩ የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓል ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም መኩሪያ በበኩላቸው ባንኩን እ.ኤ.አ በ2025 በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግም በተለያዩ የውጭ አገራት ቅርንጫፎችን የመክፈት ስራዎች እየተሰራ መሆኑን ይናገራሉ።

በመርሃ ግብሩም በዓሉ በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ቅርንጫፎች ግንባታ መሰረተ ድንጋይ ማስቀመጥ፣ የእግር ጉዞ፣ በስፖርታዊ ውድድሮች፣ በኪነ ጥበብ ውድድሮች፣ በደም ልገሳ፣ አውደ ርዕይ እና ሌሎች ፕሮግራሞች ይከበራል።

ከዚህ ውስጥም በደቡብ ሱዳንና በጅቡቲ ቅርንጫፎች መከፈታቸውን ጠቅሰው በቅርቡ በካርቱምም ተመሳሳይ ቅርንጫፍ እንደሚከፈት ተገልጿል።

 

ምንጭ፦ ኢዜአ