ኢትዮጵያ ከአውስትራሊያ፣ ኒውዝላንድና ደቡብ ኮሪያ ጋር ቢዝነስ ፎረሞችን አካሄደች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 18፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ ከአውስትራሊያ፣ ኒውዝላንድና ደቡብ ኮሪያ ጋር የቢዝነስ ፎረሞችን አካሂዳለች።

የቢዝነስ ፎረሞቹ በዛሬው እለት የተካሄዱ ሲሆን፥ በሁለት የተለያዩ መድረኮች ነው የተካሄደው።

በመጀመሪያው መድረክም የኢትዮ-አውስትራሊያ-ኒውዚላንድ የቢዝነስ ፎረም የተካሄደ ሲሆን፥ በፎረሙ በሀገራቱ መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነቶች የሚያሰፉ ውይይቶች ተደርገዋል።

በፎረሙ ላይ የተገኙት የንግድ ሚኒስትር ዶክተር በቀለ ቡላዶ፥ ፎረሙ የሀገራቱን ግንኙነት በንግድና ኢኮኖሚ የተቃኘ ለማድረግ ጉልህ አስትዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ethio_australia_2.jpg

ኢትዮጵያ በግብርና መቀናባበሪያ፣ በጨርቃ ጨርቅ፣ በቆዳ ውጤቶችና በሃይል ማመንጫ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንደሆነች ያስረዱ ሲሆን፥ የአውስትራሊያና የኒውዝላንድ ባለሀብቶች እድሉን እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ የአውስትራሊያ አምባሳደር ማርክ ሳዌርስ በበኩላቸው ፎረሙ ኢትዮጵያና አውስትራሊያ ጠንካራ የኢኮኖሚ ሸሪክ ለመሆን የሚያደርጉት ጥረት ማሳያ ነው ብለዋል።

አገራቸው በግብርና፣ በታዳሽ ኃይል፣ በመሰረተ ልማት ግንባታና በማዕድን ዘርፍ ያላትን እምቅ ልምድ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗንም ጠቅሰዋል።

በተያያዘ ዜና ኢትዮ-ደቡብ ኮሪያ ቢዝነስ ፎረምም በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ተካሄዷል።

ethio_south_korea_2.jpg

በዚህም በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ የኢትዮጵያና የደቡብ ኮሪያ ኩባንያዎች የተሳተፉ ሲሆን፥ ፎረሙ የሁለቱን ሀገራት የንግድ፣ የኢንቨስትመንት እና የሁለትዮሽ ግንኙነት እንደሚያሳድግ ይታመናል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል፥ የደቡብ ኮሪያ የቢዚነስ ቡድን ኢትዮጵያን መጎብኘት የሁለቱን ሀገራት የንግድ እና የህዝብ ለህዝብ ግንኝነት ለማጠናከር ጉልህ ድርሻ አለው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በቀላል ማምረቻ ዘርፍ እና ብዙ የሰው ሀይል የሚያሰማሩ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ፣ የቆዳ ውጤቶች፣ በግብርና ማቀነባበሪያ እና ሌሎች ዘርፎች ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ገልፀዋል።

የደቡብ ኮሪያ በቡሳን ከተማ የኢኖቬሽን ቢዝነስ ሊቀመንበር ኪም ሰንግ ጅን በበኩላቸው ኢትዮጵያ እና ደቡብ ኮሪያ በጋራ ተጠቃሚ የሚያደርገው ዘርፎችን በመለየት አብረው ለመስራት ግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ዘርፍ ማህበራት እና የኢኖቬሽን ቢዝነስ ማህበራት የሁለቱን ማህበር ግንኙነት እና የሁለቱን አገራት ንግድ እንቅሲቃሴ ለማሰደግ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።