ኢንሹራንስ በገቡ ተሽከርካሪዎች ላይ አደጋ ሲደረስ ምላሽ እስኪሰጥ ምትክ መኪና የማቅረብ አገልግሎት ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 14፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ኢንሹራንስ የተገባላቸው የቤት አውቶሞቢሎች አደጋ ሲደርስባቸው፥ የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ ምላሽ እስኪሰጥ ምትክ መኪና የማቅረብ አገልግሎት ተጀመረ ።

ዘ አልትሜት ኢንሹራስ ብሮከር የተባለው ድርጅት፥ “ይህን አገልግሎት የምሰጠው ግን በእኔ አግባቢነት የኢንሹራንስ ውልን ከመድን ሰጭ ኩባንያዎች ጋር ለፈረሙ ደንበኞቼ ነው” ብሏል።

የአገልግሎቱ ስያሜም ምትክ እንደሚባልም የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ ምግባር ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ጠቅሰዋል።

አቶ ተስፋዬ እንደገለፁት ይህ አገልግሎት በኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ የሚተገበር ነው።

ይህም በድርጅቱ በኩል ከሀገር ውስጥ መድን ሰጭ ኩባንያዎች ጋር የመድን ውል የፈረሙ ተገልጋዮች የቤት አውቶሞቢሎቻቸው እንደ ግጭት አይነት አደጋዎች ሲያጋጥሟቸው ውል ከገቡበት መድን ሰጪ ኩባንያ መኪናቸው ተሰርቶ እስኪወጣ ወይንም መኪናው ሙሉ ለሙሉ ከጥቅም ውጭ ሆኖ ጥሬ ገንዘብ ካሳ እስኪከፈለቸው ድረስ፥ የእለት ተእለት ስራቸው እንዳይስተጓጎል ምትክ መኪና ይቀርብላቸዋል ተብሏል ።

ይህን አገልግሎት ከድርጅቱ የሚያገኙት ግን በመኪናው ላይ የደረሰው አደጋ ካሳ የሚያስከፍል እስከሆነ ብቻ መሆኑም ተጠቅሷል።

ለዚህ አግልሎት የሚሆኑ መኪናዎች እንደተዘጋጁም ጠቅሰዋል።

በሂደት ለጭነት መኪናዎችም አገልግሎቱን ለመጀመር እንሰራለን ነው ያሉት።

በዘ አልትሜት ብሮከር በኩል ይህ አገልግሎት የሚሰጠው የድርጅቱ አባል በመሆንና ለዚህም ሲባል በሚከፈል ዓመታዊ የአባልነት መዋጮ ነው ብለዋል አቶ ተስፋዬ።

ክፍያውም በዓመት አንዴ ለብሮከር ድርጅቱ የሚከፈል ይሆናል።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በ2009 ዓ.ም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር አረቦን ሰብስበዋል።

ከዚህ ውስጥ 7 ነጥብ 1 ቢሊየን ብሩ ህይወት ነክ ካልሆኑ የመድን ዘርፎች የተሰበሰበ ነው።

ከ7 ነጥብ 1 ቢሊየን ብሩ ደግሞ 56 በመቶው ለተሽከርካሪዎች ሲባል የተሰበሰበ አረቦን ነው።

በሌላ በኩልም በተመሳሳይ ዓመት ከተከፈለው 3 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ካሳ ውስጥ ከ65 በመቶው በላይ ለተሽከርካሪዎች የተከፈለ ነው።

ከዚህ አንጻርም ለተሽከርካሪ መድን ገቢዎች ይህን አገልግሎት ማቅረብ ተገቢ መሆኑ ተነስቷል።

በሌላ በኩል የዘ አልትሜት ኢንሹራስ ብሮከር፥ ሎሌ የተሰኘ አገልግሎት መጀመሩን ያሳወቀ ሲሆን፥ በዚህ አገልግሎት ድርጅቱ የደንበኞቹን የካሳ አፈጻጸም ሂደት እንደ ደንበኞቹ በመሆን እንደሚያስፈፅም ገልጿል።

ይህም “የኢንሹራነስ ኩባንያ ደንበኞች መደበኛ ስራቸው ላይ ብቻ አተኩረው እንዲቀጥሉ አስችላለሁ፤ የካሳ ክፍያ ሂደትም አቀላለሁ” ብሏል ድርጅቱ።

 

በካሳዬ ወልዴ