በመዲናዋ 533 ሺህ ያህል የእንስሳት ቆዳዎች ተረካቢ አጥተው ተከማችተው ተገኝተዋል

አዲስ አበባ፣ ህዳር 14፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ 533 ሺህ ያህል የእንስሳት ቆዳዎች ተረካቢ አጥተው ተከማችተው ተገኝተዋል።

በህዝባዊ በዓላት ሰሞን የቆዳና ሌጦ ብክነት በስፋት መመልክት የተለመደ ሆኗል።

ለዚህም ሰዎች ስጋውን ወስደው ቆዳውን የመጣላቸው ምክንያት የቆዳ ዋጋ በመውረዱ እና ለነጋዴ ለማስረከብ የሚወጣውን ጉልበት እንኳን መሸፈን ባለመቻሉ ነው።

የኢትዮጵያ ቆዳና ሌጦ አቅራቢዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ አባተ እንደሚሉት፥ ቆዳ እንደ ተረፈ ምርት በመጣሉ በዘርፉ ሲተዳደሩ የነበሩ ነጋዴዎች ከስራ ውጭ እስኪሆኑ ድረስ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

በዚህም የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢስቲቲዩት ከእንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ሚኒስቴር ጋር ባደረጉት የመስክ ምልከታ፥ በአዲስ አበባ ብቻ የሚገኙ 12 የቆዳና ሌጦ ማከማቻ መጋዘን ውስጥ በርካታ ቆዳ እና ሌጦ ለፋብሪካ ሳይበቃ መበላሸቱን አረጋግጠዋል።

በዚህ ምልከታ 195 ሺህ የበግ እንዲሁም 58 ሽህ የፍየል ሌጦ እና ሌሎች የእንስሳት ቆዳዎችን ጨምሮ በድምሩ 533 ሺህ ያህል ጥሬ ምርት ተረካቢ አጥቶ ተከማችቶ ተገኝቷል ነው የተባለው።

ከዚህ ውስጥ 92 ሺህ ያህሉ ለብልሽት መዳረጉን በቅኝቱ አረጋግጠዋል።

የመበላሸቱ ምክንያት ደግሞ በሀገሪቱ ያሉ የቆዳ እና ሌጦ ማዘጋጃ ፋብሪካዎች በቂ ባለመሆናቸው እና ያሉትም አቅማቸው ውስን በመሆኑ ምርቱን በዱቤ እንዲያስረክቡ በመጠየቃቸው ለኪሳራ በመዳረጋቸው ነው ተብሏል።

በአፍሪካ በእንስሳት ሃብት ብልጫዋ ብዙ የሚባልላት ኢትዮጵያ፥ ቁጥሩን ከመጥቀስ ባለፈ አምራቹ የሚያገኘው ጥቅም እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከቆዳ እና ከቆዳ ውጤቶች የተገኘው ገቢ ያሳያል።

የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንዱ ለገሰ እንደነገሩን፥ የቆዳ አልባሳቱ ዋጋ ጭማሬ ኖሮትም ዘርፉ ያስገባው ግን ከ33 ሚሊየን ዶላር አልዘለለም።

ለቆዳና ሌጦ ዋጋ መውረድ እንደ አንድ ምክንያት የሚጠቀሰው ደግሞ የጥራት መጓደል ሲሆን፥ ይህም ቆዳውን አዘጋጅተው ለገበያ በሚያቀርቡት ላይ የራሱን ጫና እያሳደረ ነው።

በዘርፉ ከተሰማሩት ባለሃብቶች አንዱ የሆኑት አቶ ፍቅር ክፍሉ፥ በቆዳ ማዘጋጀት ሂደት ውስጥ በጥራት መጓደል የሚወድቀው ምርት ቀላል የሚባል አይደለም ብለዋል።

ለዚህም ከቆዳ ኢንዱስትሪው ውስንነት በተጨማሪ በዓለም ገበያ የቆዳ ዋጋ መውረድ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ውስን አድርጎታል ሲል የእንስሳት እና ዓሳ ሃብት ሚንስቴር ገልጿል።

ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ፈቃዱ በየነ እንደሚሉት፥ በእርባታ ስርዓቱ እና በግብይቱ ሂደት ያሉት ችግሮችም ብዙ ናቸው።

በመሆኑም ችግሩን በፖሊሲ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው ሲሉ ይናገራሉ።

ሚኒስትር ዲኤታዋ ወይዘሮ ምስራቅ መኮነን በበኩላቸው፥ የፋብራካዎችን ዓቅም በተለያዩ ማበረታቻዎች ማሳደግና አጠቃላይ ዘርፉ እንዲነቃቃ ማድረግ መጀመሩን ይናገራሉ።

በአጠቃላይ ግብዓቱ የሚገባውን ዋጋ እንዲያገኝ አለማድረጉ፥ ዘርፉን ከሚመሩት የመንግስት ተቋማት እስከ ኢንዱስትሪው አንቀሳቃሾች በእቅድ አለመመራት ዋናው ችግር እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል።

በጌታሰው የሺዋስ