በበጀት አመቱ አራት ወራት 63 ቢሊየን ብር ገቢ ተሰብስቧል

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 13 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2010 በጀት አመት 230 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ያቀደው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ባለፉት አራት ወራት 63 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሞገስ ባልቻ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ ከሀምሌ 1 ቀን 2009 እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ 72 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 63 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን ተናግረዋል።

ገቢው በበጀት አመቱ ለመሰብሰብ ከታቀደው 27 በመቶ መሆኑን ጠቅሰው፥ የግብር ከፋዩ የአመለካከት ችግርና የህግ ተገዥነት አለመጎልበት ለገቢው ማነስ ዋና ምክንያት መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ባለፉት አራት ወራት የንግድ ትርፋቸውን ለገቢዎች እና ጉምሩከ ባለስልጣን ካሳወቁ 16 ሺህ ግብር ከፋዮች ውስጥ ከክፍያ ጋር ግብራቸውን ያሳወቁት 63 በመቶ ሲሆኑ፥ ወደ 28 በመቶዎቹ ደግሞ የኪሳራ ሪፖርት አድርገዋል።

ከ16 ሺህ በላይ ከሚሆኑት የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝጋቢዎች ውስጥም ከክፍያ ጋር ሪፖርት ያደረጉት 30 በመቶ ብቻ ሲሆኑ፥ 45 ከመቶ የሚጠጉት ተመላሸ ጠይቀዋል፤ 25 በመቶዎቹ ደግሞ ስራ አልሰራንም ማለታቸውን ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያነሱት።

መረጃው አሁን ላይ ካለው ሃገራዊ እውነታ ጋር ይቃረናል የሚሉት ዳይሬክተሩ፥ ከሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ ጋር ተያይዞ የሚታየውን ክፍተት ለመሙላትም በዚህ አመት ሁሉንም ግብር ከፋዮች የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ ባለቤት ለማድረግ መታቀዱን ገልጸዋል።

የኪሳራ እና ተመላሽ ጠያቂዎቹ መረጃ ትክክለኛ ስለመሆኑ እያጣራሁ ነው ያለው ባለስልጣኑ፥ ለዚህም ጠንካራ የኦዲት ስርዓት ለመዘርጋትና የሰራተኞቹን አቅም እና ክህሎት ለማሳደግ እየሰራሁ ነው ብሏል።

ዋና ዳይሬክተሩም በአዲስ አበባ እና ሌሎች የክልል ከተሞች በሚገኙ ግብር ከፋዮች ላይ በተደረገ ክትትል ያለ ደረሰኝ ግብይት ሲያከናውኑ የተገኙ 90 ድርጅቶች እና 131 ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ነው ብለዋል።

ለህግ ተገዥ ያልሆኑ ግብር ከፋዮችን ለመለየት እና ተገቢውን ግብር እንዲከፍሉ ለማድረግ ከሚሰራው ስራ ጎን ለጎንም የታክስ አስተዳደር ትራንስፎርሜሽንን ለማረጋገጥ የተለያዩ ሰራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።

ከገቢ ግብር አዋጁ መሻሻል ጋር ተያይዞ የተቀናጀ የመንግስት የገቢ አስተዳደር ስርዓት ምቹ ያልሆኑ 50 ችግሮች ተለይተው ስርዓቱን የማስተካከል ስራ እየተከናወነ ነው።

ከዚህ ባለፈም ቀደም ሲል ጥቅም ላይ ሲውል የነበረውን እስኩዳ ፕላስ ፕላስ፥ በአዲስ መልክ የሚተካ የኢትዮጵያ የጉምሩክ አስተዳደር ስርዓት በልጽጎ በአሁኑ ወቅት በቃሊቲ እና በሞጆ ጉምሩከ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብለዋል።

ስርዓቱ መልካም ውጤት ያሳየ በመሆኑ በቀጣይ በሁሉም የጉምሩክ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች ተግባራዊ ሲደረግ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮችን ይቀርፋልም ነው ያሉት ዳይሬክተሩ።

ባለስልጣኑ ግብር ከፋዮች ወደ ገቢዎች እና ጉምሩክ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት መስሪያ ቤቶች መሄድ ሳያስፈልጋቸው ግብራቸውን ማሳወቅ የሚችሉበትን በኤሌክትሮኒክስ የታገዘ የታክስ አሰራር ስርዓት (ኢ ፋይሊንግ) አሰራርንም ጀምሯል።

የኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክስን የአንድ መስኮት አገልግሎት ፕሮግራምም ቀርጿል።

በዚህም ከገቢና ወጪ ንግድ ጋር ግንኙነት ያላቸው 20 መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ጥምረት እንዲመሰርቱ ተለይተው ሶፍትዌር የማበልፀግ ስራ የተጀመረ ሲሆን፥ በዚህ አመት መጨረሻ ወደ ተግባር ይገባል ተብሏል።

 

 

 

በፋሲካው ታደሰ