በኮምቦልቻ ከተማ የተገነባው የከባድ መኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ ሥራ ጀመረ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 13 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ወሎ ዞን ኮምቦልቻ ከተማ የተገነባው የከባድ መኪና አካላት መገጣጠሚያ ፋብሪካ ሥራ ጀመረ።

አላሚ ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ በሚል ስያሜ የሚጠራው ፋብሪካ በ200 ሚሊየን ብር ካፒታል የተገነባ ሲሆን፥ የተለያዩ የተሽከርካሪ አካላትን እንደሚያመርት ተገልጿል። 

የፋብሪካው ሥራ አስኪጅ አቶ ጌታወይ ይርጋ እንዳሉት፥ ፋብሪካው የከባድ መኪና ተሳቢ፣ ከፍተኛ ጭነት ሟጓጓዣ (ሎቤድ)፣ የነዳጅ ማጓጓዣ ቦቴና መሬት ውስጥ የሚቀበር የነዳጅ ታንከር በማምረት ይገጣጥማል፡፡

ካለፈው ጳጉሜን ወር 2009 ዓ.ም ጀምሮ 26 ሎቤዶችን፣ 15 ተሳቢዎችንና አራት የነዳጅ ማጠራቀሚያ ገንዳ (ታንከሮችን) ማምረቱን ጠቅሰው፥ በአሁኑ ወቅት ፋብሪካው በኃይል እጥረት ምክንያት 20 በመቶ አቅሙን ብቻ እየተጠቀመ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ወደፊት በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር በቀን አምስትና ከዚያ በላይ የከባድ መኪና አካላትን መስራት እንደሚችል አመልክተዋል።

በ20 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ የተገነባው ፋብሪካ በአሁኑ ወቅት ለ100 ሰዎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል።

ፋብሪካው በሃገር ውስጥ የሚያመርተው ምርት የውጭ ምንዛሪን ከማስቀረት ባለፈ የቴክኖሎጂ ሽግግሩን በመደገፍ በኩል የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ተመልክቷል፡፡


ምንጭ፦ ኢዜአ