የቻይና ሁናን ግዛት ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በወርቅና ብረት ማዕድን ዘርፍ መሰማራት እንደሚፈልጉ ገለፁ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 12፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይና ሁናን ግዛት ልዑካን ቡድን በማዕድን ዘርፍ ለመሰማራት ከማዕድን፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ጋር ዛሬ ምክክር አድርገዋል።

በሚስተር የ ዶንግሶንግ የሚመራው የቻይና ሁናን ግዛት ልዑካን ቡድን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በመገኘት ባደረጉት ውይይት፥ በወርቅና የብረት ማዕድናት ዘርፍ ላይ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ የማዕድን ሃብትን በስፋት ለማልማት ባላት እቅድ ላይ በልምድ ልውውጥ እና በቴክኖሎጂ ለማገዝ ፍላጎት እንዳላቸውም ልዑካኑ አብራርተዋል።

የግዛቷ እና የቻይና ባለሃብቶች አሁን ካላቸው ተሳትፎ በላቀ ሁኔታ በማዕድንና በሌሎች ዘርፎች እንዲሰማሩ በመንግስት በኩል እድሎች እየተመቻቹ መሆኑን የማዕድን፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ ጠቁመዋል፡፡

ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ቴዎድሮስ ገብረ እግዚአብሔር በበኩላቸው፥ ቻይና በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ አሻራዋን እያሳረፈች ያለች ሃገር መሆኗን ነው ለልዑካን ቡድን የገለፁት።

በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተው አጋርነት የበለጠ መጠናከር እንደሚገባውም አቶ ቴዎድሮስ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ከሁናን ግዛት ጋር ያላት ግንኙነት በጋራ መስራት የሚያስችሉ አበይት ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ነው ሚኒስትር ዲኤታው ያብራሩት።

 

 

መረጃውን ያገኘነው ከማዕድን፣ ነዳጅ እና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ነው።